የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አራዳ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሲኒማ ራስ (ደጎል)አደባባይ የሚገኘውን የሁለት የጉዞ መስመሮች የታክሲ መጫኛ ማውረጃ ቦታ ለውጥ አደረገ፡፡

አዲስ አበባ፣ ህዳር 20፤ 2015 ዓ.ም፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ አራዳ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ለረጅም ጊዜ የታክሲ መጫኛና ማውረጃ የነበረውን የሲኒማ ራስ (ደጎል) መጫኛና ማውረጃ የሚገኘውን ከፒያሳ ካዛንቺስና ከፒያሳ በካዛንቺስ ሀያ ሁለት መገናኛ የጉዞ መስመሮች የቦታ ለውጥ በማድረግ ወደ ደጎል አደባባይ በታች በተለምዶ ግሎርየስ (ጣይቱ ሆቴል) አካባቢ የታክሲ የመጫኛ ማውረጃ ቦታ ለውጥ አደረገ፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የአራዳ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ሰብስባቸው መንግስቴ ቀደም ሲል አገልግሎቱ ሲሰጥበት ከነበረው ቦታ መቀየር ያስፈለገው በቦታው የህዝብ ትራንስፖርት ተጠቃሚው ቁጥርና አገልግሎቱ የሚሰጥበት ቦታ ባለመመጣጠኑ ከፍተኛ የሆነ የተሽከርካሪና የሰው መጨናነቅ በመፍጠሩ መሆኑን በመግለፅ፤ የቦታ ለውጥ ከመደረጉ በፊት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ ከትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ማዕከላዊ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት፣ ከአራዳ ትራፊክ ፖሊስ ፅ/ቤት እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ውይይት በማድረግ አስፈላጊውን የትራፊክ ምልክትና ማመላከቻ በመትከል ስራው ከቀን 19/03/2015 ጀምሮ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡

የአራዳ ክፍለ ከተማ ትራፊክ ጥበቃ ቁጥጥር ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ቢኒያም ከበደ የቅድመ ዝግጅት ስራው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመሰራቱ ወደ ትግበራ ለመግባት አልተቸገርንም ብለዋል፡፡

ዋና ኢንስፔክተሩ አያይዘውም ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል እየሰራ ያለው ስራ እጅግ አበረታች መሆኑን ገልፀዋል።

የትራንስፖርት ተጠቃሚው ማህበረሰብም ቀደም ሲል ከነበረው የታክሲ መጫኛና ማውረጃ ቦታ የተሻለ በመሆኑ ለትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮል ብለዋል።

Leave a Reply