በትራንስፖርት ቢሮ 9417 በነፃ የስልክ ጥሪ እየቀረቡ ያሉ የህዝብ ቅሬታዎች ምላሽ እየተሰጠባቸው መሆኑ ተገለፀ፡፡

አዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ፤ ሰኔ 19/ 2015 ዓ.ም)

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖት ቢሮ በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡ ዙሪያ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ባዘጋጀው ነፃ የስልክ ጥሪ መስመር 9417 ጥቆማዋችን በመቀበል ለህዝብ ቅሬታዎች ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ገልጿል፡፡

በቢሮው የነፃ የስልክ ጥሪ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ፍቃዱ ጫላ እንደተናገሩት በበጀት ዓመቱ በነፃ መስመር ስልክ የቀረቡ የህዝብ ቅሬታዎች መፈታታቸውን ገልፀዋል፡፡

በነጻ የስልክ መስመሩ በድግግሞሽ የሚቀርቡ ቅሬታዎቹም የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች መስመር ማቆራረጥ፣ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፣ መሳደብ እና ከተፈቀደው የመጫን አቅም በላይ በመጫን ተሳፋሪ ማጉላላት ሲሆኑ ሌሎችም ከተጠሪ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥና መረጃ ለመጠየቅ ወደ ጥሪ ማዕከሉ እንደሚደወል አስተባባሪው አስታውቀዋል፡፡

እነዚህን ጥቆማዎች መነሻ በማድረግም፤ ጥቆማው ወደ ተሰጠበት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት መረጃውን በመላክ ቅሬታ አቅራቢውና ቅሬታ የቀረበበት አካል በአካል ወይም በስልክ በጉዳዩ ላይ እንዲተማመኑና አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ እየተሰራ ሲሆን ህብረተሰቡም ከህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡ ጋር ተያይዞ ለሚኖረው አስተያየትና ጥቆማ ወደ ማዕከሉ ስልክ ሲደውሉ ጥፋት ያጠፋውን ተሽከርካሪ ሰሌዳ፣ የጉዞውን መነሻና መድረሻ እንዲሁም ሰዓቱን ጭምር መረጃ በመያዝ እንዲያቀርብ ተጠቁሟል፡፡

ዘገባው፦ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ነው

ለበለጠ መረጃ፦ 011-666- 33-74/

ነጻ የስልክ መስመር 9417

Web:-aactb.gov.et ይጠቀሙ!

Leave a Reply