የአዲስ አበባ ትላልቅ ገፀ-በረከቶች (#1)

ግዙፍ የመንገድ መሰረተ-ልማት በአዲስ አበባ

የአዲስ አበባ ከተማን የመንገድ መሠረተ-ልማት ለማስፋፋትና ለማዘመን የነባር መንገዶች ማሻሻያ እና የአዳዲስ መንገዶች ግንባታ እየተከናወነባቸው ከሚገኙ አካባቢዎች አንዱ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ነው፡፡

በደቡባዊው የአዲስ አበባ ክፍል በራስ አቅምና በኮንትራት እየተገነቡ የሚገኙት ሦስት የመንገድ ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ ከ26.9 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው ሲሆኑ፣ ከ25 እስከ 60 ሜትር በሚደርስ የጎን ስፋት በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከ5.4 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነቡ ከሚገኙ ሦስት የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል

(1). የደቡብ አዲስ አበባ የመንገድ መሠረተ-ልማት ግንባታ ፈርጥ የቃሊቲ – ቡልቡላ – ቅሊንጦ አደባባይ የመንገድ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት 10.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና ከ40 እስከ 60 ሜትር የጎን ስፋት ያለው አዲስ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ነው፡፡

ፕሮጀክቱ የከተማዋን የኢንዱስትሪ ፓርክ በመንገድ መሠረተ-ልማት የሚያስተሳስርና በቱሉ ዲምቱ የክፍያ መንገድ አቅጣጫ ወደ ከተማዋ ለሚገቡና ለሚመጡ ተሸከርካሪዎች የወጪ ገቢ ኮሪዶር ሆኖ የሚያገለግል ዋና መንገድ በመሆኑ በቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ መንገድ ላይ የሚኖረውን የትራፊክ ጫና ያቃልላል፡፡

በተጨማሪም በኮዬ ፈጬ እና አካባቢው ባሉ የጋራ መኖሪያ መንደሮችና በዙሪያው ያሉ ነዋሪዎች በአቋራጭ ወደ መሃል ከተማ እንዲጓጓዙ የሚያስችል መንገድ በመሆኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍ ያለ ነው፡፡

በቡልቡላና አቃቂ ወንዞች ላይ የተገነቡትን እና በድምሩ ግማሽ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸውን ግዙፍ የወንዝ መሻገሪያ ድልድዮች ጨምሮ፣ በሦስት ቦታዎች ላይ የተገነቡት 128 ሜትር ርዝመት ያላቸው የተሸከርካሪ መሻገሪያ ድልድዮች የመንገድ ፕሮጀክቱ ተጨማሪ ድምቀቶች ናቸው፡፡

ቀደም ሲል የመንገድ መሠረተ-ልማት ባልተዘረጋበት ሥፍራ የተገነባው የቃሊቲ – ቡልቡላ – ቅሊንጦ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በከተማዋ እየተገነቡ ከሚገኙ አዳዲስ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል የሚጠቀስ ሲሆን፣ አሁን ላይ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈፃፀም 85 በመቶ ላይ ደርሷል፡፡

(2). በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከሚገነቡት መንገዶች መካከል የቃሊቲ – ቱሉዲምቱ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ሲሆን ከአገልግሎት ብዛት እጅግ በጣም የተጎዳና 10 ሜትር ስፋት የነበረውን የመንገድ ስፋት ወደ 50 ሜትር የመንገድ ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ የተገነባ ነው፡፡

መንገዱ የገቢና ወጪ ንግድ የሚከናወንበት ኮሪደር እንደመሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የትራፊክ እንቅስቃሴ ማስተናገድ በሚችል ሁኔታ በአንድ ጊዜ በሁለቱም አቅጣጫ 8 መኪናዎችን ማስተናገድ እንዲችል ተደርጎ የተገነባ መንገድ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የመንገድ መስመሩ በሚያልፍባቸው የመንገድ መጋጠሚያዎች ላይ የሚፈጠረውን የትራፊክ መጨናነቅ ችግር የሚፈቱና በአጠቃላይ 350 ሜትር ርዝመት ያላቸው ሦስት የትራፊክ ማሳለጫ ተሸጋጋሪ ድልድዮችን አካቶ እንዲገነባ ተደርጓል፡፡

መንገዱ የአዲስ አበባ ከተማ የጭስ አልባ ትራንስፖርትን በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር ባቀደችው መሰረት 11 ኪ.ሜ. ርዝመት ያለውን የብስክሌት መሰረተልማት ግንባታን እንዲሁም ለእግረኛ እንቅስቃሴ ምቹና በቂ ስፋት እንዲኖራቸው ተደርገው የተገነቡ የእግረኛ መንገዶች ተካተውበታወል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በቀጣይ ምዕራፍ ለሚገነባው የብዙሀን ትራንስፖርት መሰረተ ልማት ታሳቢ ባደረገ መልኩ የ11.2 ሜትር ስፋት ያለው የመንገድ አካፋይ እንዲኖረው ተደርጓል።

ፕሮጀክቱ በተፈለገው ፍጥነት እንዳይከናወን ከወሰን እና ከፋይናንስ ጋር የተያያዙ ችግሮች ፈተና የነበሩ ቢሆንም ችግሮቹ እንዲፈቱ የከተማ አስተዳደሩ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ቀሪው የፕሮጀክቱ የግራ ክፍል በፍጥነት በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡

አሁን ላይ የመንገዱን የግራ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ አስፋልት በማልበስ በአጭር ጊዜ ሙሉ በሙሉ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡

(3). ሌላው የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የመንገድ መሠረተ-ልማት ፀጋ የአቃቂ ቶታል – ቱሉዲምቱ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ቀደም ሲል ተገንብቶ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየውን የአቃቂ ከተማና አካባቢውን ነባር መንገድ ማሻሻል ታላሚ ያደረገ ሲሆን፣ 5.2 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 25 ሜትር የጎን ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ እየተገነባ የሚገኝ ነው፡፡

አሁን ላይ ወደ መጠናቀቂያ ምዕራፍ እየተሸጋገረ የሚገኘው የቃሊቲ ቶታል – ቱሉዲምቱ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አስፋልት የማልበስ ሥራ እየተከናወነ ሲሆን፣ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈፃፀምም 86.3 በመቶ ላይ ደርሷል፡፡

የቃሊቲ ቶታል – ቱሉዲምቱ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ህብረተሰቡ ለረጂም ጊዜያት ሲያቀርብ የነበረውን የመንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄ የሚመልስ ከመሆኑም ባሻገር፣ የአቃቂ ከተማን እድገት በማፋጠን ለአካባቢው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ይታመናል፡፡

Leave a Reply