ከተማዋን የሚመጥን የትራንስፖርት ስርዓት ለመዘርጋት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተገለፀ።

(የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ፤ ሰኔ 15/2016 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ያብባል አዲስ ዛሬ ተጠሪ ተቋማት ከሆኑት የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን እና ከአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የስራ ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት የትውውቅ መድረክ ከተማዋን የሚመጥን የትራንስፖርት ስርዓት ለመዘርጋት ትኩረት ተሰጥቷ መስራት ይገባል ብለዋል።

በመድረኩም የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣንና የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን የስራ ኃላፊዎች በአዋጅ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት፣ አገልግሎት አሰጣጥ፣ ከሪፎርሙ አንፃር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትና የመጡ ውጤቶች እንዲሁም በዘርፉ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ያብባል አዲስ ከተማ አስተዳደሩ ለትራንስፖርት ዘርፉ ትልቅ ትኩረት የሰጠው በመሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን የሚስተዋለውን የትራንስፖርት ችግር በጥናት በመደገፍ የህግ ማእቀፎችንና አደረጃጀቱን በመፈተሽ፣ በሰለጠነ የሰው ሀይል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚገባ በአንክሮ ገልፀዋል።

ኃላፊው አክለውም በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ያለውን ፍላጎት ማጣጣም፣ የBRT ኮሪደርን ማልማት፣ የህዝብ ትራንስፖርት ኦፕሬተሮች አደረጃጀት መፈተሽ፣ የትራፊክ ደህንነትና ፍሰት ማሳለጥ፣ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ኢንስፔክሽንንና የመረጃ አያያዝ ስርዓታችንን ማጠናከር እንደሚገባ ገልፀዋል።

በመጨረሻም ከተማዋን የሚመጥን የትራንስፖርት ስርዓት ለመፍጠር፤ አመራሩ በአገልጋይነት መንፈስ ትራንፎርሜሽናል አመራር በመሆን ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ በትውውቅ መድረኩ ተገልፆል።

Leave a Reply