የከተማ አስተዳደሩ የመንገድ አውታሮችን ከማስፋፋት ጎን ለጎን የትራፊክ አደጋ እንዲቀንስ የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችን በማልማት እና በማስፋት ትኩረት አደርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ::

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ በአለማቀፍ ደራጀ ለ17ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ15 ኛ ጊዜ የሚከበረውን የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች ማስታወሻ ቀን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካሂደ፡፡

በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ የከተማ አስተዳደሩ የመንገድ አውታሮችን ከማስፋፋት ጎን ለጎን የትራፊክ አደጋ እንዲቀንስ የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችን በማልማት እና በማስፋት ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ በመግለፅ፤ በከተማዋ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የተጀመሩ በጎ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች ቀን በዋነኝነት የምናከብረው የተጎዱ ወገኖቻችንን ለማሰብ ፣ ለጉዳቱ መንስኤ የሆኑትን ለመከላከል እና ጉዳቱን ያስከተሉ አካላት ተጠያቂ የሚሆኑበትን አሰራር ለመዘርጋት ነው ብለዋል።

የትራፊክ አደጋ በጤና ተቋማት እና ባለሙያዎች ላይ እያሳደረ ስላለው ተጽእኖ የመነሻ ጽሁፍ በፕሮፌሰር ብሩክ ላጲሶ ለመርሃ ለፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች የቀረበ ሲሆን በአደጋው የሚከሰተውን ሞት ለመቀነስ ቅድመ ሆስፒታል በተለይ የአምቡላንስ ተሽከርካሪዎችን በህክምና ቁሳቁስ በሟሟላት እና የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ማሰማራት እንደሚያስፈልግ የቢሮ ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

በመርሀ ግብሩም ላይ በሆስፒታሉ በህክምና ላይ የሚገኙ የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች ጉብኝት የተካሄደ ሲሆን ጉብኝቱ ሰዎች ከትራፊክ አደጋ በኋላ የሚያጋጥማቸውን አካላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳት በመረዳት ለቀጣይ ስራዎቻችን ትልቅ ሚና ይኖረዋል ሲሉ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚደቅሳ ተናግረዋል፡፡

የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የመንገድ ደህንነት ካውንስል ተቋቁሞ እና የመንገድ ደህንት ስትራቴጂ ተነድፎ ስራዎች እየተከናወኑ በመሆኑ አበረታች ውጤቶች እየመዘገቡ ቢሆንም የባለድርሻ ተቋማት፣ አጋር ድርጅቶች በተለይ ሚዲያዎች ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ረገድ በደንብ ሊሰራበት እንደሚገባ አቶ ክበበው ጠቁመዋል።

ፕሮግራሙ አፒያሳ አራዳ ህንጻ መነሻ ያደረገ በማርሽ ባንድ የታጀበ የመንገድ ደህንነት ግንዛቤ ማስጨበጫ እና የግር ጉዞ እስከ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የተደረገ ሲሆን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በህክምና ላይ ለሚገኙ የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች የአዲስ አበባ በጎ ፈቃደኛ የትራፊክ አስተናባሪዎች የደም ልገሳ አድርገዋል።

በፕሮግራሙ ላይ የሻማ ማብራት እና የፓናል ውይይት ተደርጎ በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ ፕሮግራሙ ተጠናቋል።

Leave a Reply