አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17/2015 ዓ.ም፤ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ እና የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተስፋዬ ኦሜጋ በጋራ በመሆን በጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ወረዳ አንድ የቤት እድሳት መርሃ-ግብሩን በይፋ አስጀምረዋል።
በመርሃ-ግብሩም የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ በ 2015 ዓ.ም በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣንና በስሩ ያሉ ተቋማትን በማስተባበር ከ 1.8 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የ 6 አቅመ ደካማ መኖሪያ ቤቶችን በወረዳ 1 (አንድና) 6 (ስድስት) ያስገነባል ብለዋል፡፡
ኃላፊው አክለውም በዚህ የበጎ ፍቃድ ስራ ላይ ለተሳተፉ አካላት ምስጋና አቅርበው በተለይ የአዲስ አበባ አሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ማህበር ላደረገው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ምስጋና ሊቸረው ይገባል ብለዋል፡፡
የሚገነቡትንም ቤቶች በተቀመጠው ጊዜ ሰሌዳ መሰረት ተጠናቀው ለነዋሪዎቹ ርክክብ የሚፈጸም ሲሆን፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በ 2014 በጀት ዓመት በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ 4 ቤቶችን አስገንብቶ ማስመረቁ ይታወሳል።