(የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ፤ ግንቦት 13/2016 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የትራንስፖርት ስምሪት አገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል የተገልጋዩን እርካታ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የህዝብ ትራንስፖርት አደረጃጀትና የስምሪት ዳይሬክቶሬት አሳውቋል፡፡
ዳይሬክቶሬቱም በዋናነት የኦፕሬተርነት ፈቃድና እድሳት፣ የስምሪት ፍቃድና የህዝብ ትራንስፖርት ባለንብረቶች ማህበራትን ማደረጀት የሚሰጥ ሲሆን አገልግሎቱንም በተቀመጠው ስታንዳርድ መሰረት እየሰጠ ይገኛል፡፡
የህዝብ ትራንስፖርት አደረጃጀትና የስምሪት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አሸናፊ ስዩም ዳይሬክቶሬቱ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ስምሪት አሰጣጡ ፍትሀዊ እንዲሆን የኮድ 3 የሚኒባስ ድጋፍ ሰጪ ተሽከርካሪዎች በየሶስት ወሩ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የሽክርክሪት አገልግሎት እንዲሰጡ የአሰራር ስርዓት መዘርጋቱን ገልፀው፤ በቀጣይም የህዝብ ትራንስፖርት የድጋፍ ሰጪ መካከለኛ አውቶብሶች ወይም ሚዲባሶች በተመሳሳይ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ኃላፊው አክለውም አሁን በተደረገው ሪፎርም መነሻነት ህብረተሰቡ በቴክኖሎጂና በሲስተም የተደገፈ ዘመናዊ አገልግሎት እንዲያገኝና አሁን እየተሰጠ ያለውን የማንዋል አገልግሎት አሰጣጥ በክፍሉ ለማስቀረት ዳይሬክቶሬቱ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በዳይሬክቶሬቱም የውስጥ አቅም በለማ ቴክኖሎጂ እያንዳንዱ ተገልጋይ አገልግሎቱን በምን ያህል ደቂቃ ማግኘት እንደቻለ እየተገመገመ እንደሆነና ይህም ለአገልግሎት አሰጣጡ መሻሻል ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የህዝብ ትራንስፖርት አደረጃጀትና የስምሪት ዳይሬክቶሬት አሳውቋል።