ህብረተሰቡ የትራንስፖርት መሰረተ-ልማት ሀብቶችን መጠበቅ እንደሚገባው ተገለፀ።

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 13፤ 2015 ዓ.ም፤ የትራንስፖርት መሰረተ-ልማት ሀብቶች ለታለመላቸው አገልግሎት እንዲውሉ ህብረተሰቡ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ሀብቶችን ከስርቆትና ከጉዳት የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ገልፆል።

በቢሮው የመሰረተ-ልማት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ካሳዬ እምሬ የትራንስፖርት መሰረተ-ልማት ሀብቶች ከፍተኛ መዋለ ነዋይ የፈሰባቸው የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የጋራ ሀብት መሆኑን በመግለፅ፤ ሀብቶች በተገቢው መንገድ ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ከስርቆትና ብልሽት ለመጠበቅም ቢሮው በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

ነገር ግን በአንዳንድ አከባቢዎች በተለይ ከቅርብ ወራት ወዲህ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ሀብት የሆነውን የአውቶብስ መጠለያዎች ላይ እየተከሰተ ያለው የስርቆት ወንጀል ትክክል አለመሆኑንና በአስቸኳይ መቆም እንደሚገባው ወ/ሮ ካሳዬ አበክረው ገልፀዋል፡፡

የስርቆት ወንጀሉን ሲፈፅሙ በተገኙ ወንጀለኞች ላይ አስተማሪ ቅጣት እንዲጣልባቸው የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑንና ህብረተሰቡም ወንጀለኞች ለህግ እንዲቀርቡ ተባባሪ እንዲሆን ዳይሬክተሯ ጥሪያውን አቅርበዋል ።

በመዲናዋ ከዚህ በፊት በተመረጡ ቦታዎች አንድ ሺህ (1000) የአውቶብስ መጠበቂያ መጠለያዎች የነበሩ ቢሆንም ሀምሳ ሁለቱ (52) በተለያዩ የልማት ስራዎች በመነሳታቸው አሁን ዘጠኝ መቶ አርባ ስምንት (948) የአውቶቡስ መጠበቂያ መጠለያዎች ለህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚዎች በአግባቡ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

በመጨረሻም ህብረተሰቡ በትራንስፖርት መሰረተ-ልማት ሀብቶች ላይ የስርቆት ወንጀልና ጉዳት ሲፈፀም ሲመለከት በአቅራቢያው ለሚገኙ የፖሊስና የፀጥታ አካላት እንዲሁም የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤትና በነፃ የስልክ መስመር 9714 ጥቆማ መስጠት እንደሚቻል ቢሮው ያሳውቃል፡፡

ዘገባው፦ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ነው

ለበለጠ መረጃ፦ 0116 663374

Leave a Reply