የኮሙኒኬሽን ዘርፉን በዕውቀትና በክህሎት ለመምራት የሚያግዝ የስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ስልጠና በየደረጃው ለሚገኙ የኮሙኒኬሽን አመራሮች መሰጠት ተጀመረ

የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ከዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በየደረጃው ለሚገኙ የህዝብ ግንኙነት አመራሮች በስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን እና በመሰል ጉዳዮች ላይ የአቅም ግምባታ ስልጠና መሰጠት ተጀምሯል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ እናታለም መለሰ ፤ ስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽንን በተመለከተ በሰጡት ስልጠና አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት ፓርቲና መንግስት ያስቀመጡት አቅጣጫ ውጤታማ እንዲሆን የአስተሳሰብና የአመለካከት አንድነት ለመፍጠር የተቀናጀና የተናበበ ጥረት ከሁሉም እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።

የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ሜኤሶ ኤለማ በበኩላቸው የኮሙኒኬሽን አመራሩ ለህዝቡ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ በማድረስ ለከተማችን ልማት እና አስተማማኝ ሰላም መስፈን በጋራ እንዲረባረብ ለማስቻል በእውቀት፣ በክህሎትና በተግባራዊ እንቅስቃሴው አቅሙን እያሳደገ መጓዝ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

በህዝብ ድምፅ አሸናፊ የሆነው የብልፅግና ፓርቲ ሀሳብ ሀገር እየመራ መሆኑን ያወሱት ኃላፊው የምንገነባው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲዳብር ሁሉም ዜጋ ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን የሚፈታተኑ አፍራሽ አስተሳሰቦችን በጋራ በመመከት ብልፅግናችንን ማፋጠን እንደሚገባ አስረድተዋል።

የቢሮው ም/ሀላፊ አቶ ሁሴን ዝናቡ በበኩላቸው የኮሙኒኬሽን መዋቅሩ ተቀራራቢ አቅም እንዲኖረውና የበለጠ ተቀናጅቶ እንዲሰራ መሰል ስልጠናዎች ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን በመግለጽ በቀጣይም በየደረጃው ላሉ አመራሮች እና አባላት ይህን መሰል ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።

ምንጭ:-አ.አ ኮሙኒኬሽን ቢሮ

Leave a Reply