ለፌዴራልና ለከተማ አስተዳደር ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች ተከታታይ ስልጠናዎችን እየሰጠ ያለው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ኢፕድ) ስልጠና ማዕከል፤ ከሰባት ሺህ በላይ ለሚሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ ድርጅት አመራሮች እና ሰራተኞች የሚሰጠውን ስልጠና ትላኖት ጀምሯል።
ለድርጅቱ አመራሮችና ሰራተኞች “መልካም ስብዕና ግንባታ ለአገልጋይነት አስተሳሰብና ተግባር” የሚሰጠው ስልጠና በአምስት ዙር የሚከናወን ሲሆን፤ ዛሬ በተጀመረው በመጀመሪያው ዙር ስልጠና ከ800 በላይ አመራሮች እና ሰራተኞች ተካፋይ ሆነዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛው አለሙ በስልጠናው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “ድርጅታችን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን በቀን ያገለግላል። ይህም ማለት የድርጅቱ ሠራተኞች በቀን ከበርካታ ሰዎች ጋር ተግባቦት ያደርጋሉ ማለት ነው።
ስለዚህ የተገልጋይን አመለካከት በመገንዘብ ቀልጣፋ አገልገሎት መስጠት ያስፈልጋል። ይህንንም ይበልጥ ለማጠናከር ኢፕድ ስልጠና እንዲሰጠን ወስነናልዕ ብለዋል።
ኢፕድ አንጋፋ እና ትልቅ የሚዲያ ተቋም እንዲሁም በስልጠና ዙሪያ በቂ ልምድ ያለው ተቋም በመሆኑ ለአምስት ቀናት ከሰባት ሺህ በላይ አመራሮች እና ሰራተኞች የሚሰጠው ስልጠና በስራቸው ላይ አዎንታዊ ለውጥ ያመጣል ብለው እንደሚያምኑ ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ታደሰ በበኩላቸው፤ ኢፕድ ከአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ ድርጅት ጋር በጋራ በመስራቱ መደሰታቸውን ገልጸው፤ ኢፕድ “መልካም ስብዕና ግንባታ ለአገልጋይነት አስተሳሰብና ተግባር” በሚል ጽንሰ ሀሳብ የሚሰጠው ስልጠና ከድርጅቱ የእለት ተዕለት ስራ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመሆኑ ፋይዳው ላቅ ያለ ነው ብለዋል።
ኢፕድ በአዲስ አበባ የአውቶብስ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ያለውን ሁኔታ የሚሳዩ ታሪካዊ ፎቶዎች፣ ዜናዎች እና በርካታ ጽሑፎች ዶክመንተ አድርጎ መያዙን ጠቁመው፤ ይህንን የድርጅቱን ታሪክ በፎቶ ቡክ፣ በመጽሔት እና በዶክመንተሪ ለመያዝ በሚፈልግበት ወቅት ኢፕድ ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
ዘገባው፦የኢፕድ ነው