የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ መስከረም 9 ለሚጀመረው የ 2015 የትምህርት ዘመን ዝግጅት ማድረጉን አሳወቀ።

መስከረም7/2015ዓ.ም:-

ቢሮው ዛሬ ከቢሮው ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች፣ ከትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ፣ ከሸገርና አንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን ከትምህርት መጀመር ጋር ተያይዞ በትራንስፖርት ዘርፉ እየተሰራ ያለውን የቅድመ ዝግጅት ስራ በመገምገም፤ መስከረም 9 ለሚጀመረው የ 2015 የትምህርት ዘመን አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን አሳወቀ።

የሸገር ብዙሀን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅትም ተማሪዎች ደህንነታቸውና ምቾታቸው ተጠብቆ በሸገር የተማሪ ሰርቪስ በተመረጡ መስመሮች አገልግሎት እንዲያገኙ የቅድመ ዝግጅት ስራውን አጠናቋል።

የከተማዋን የትራፊክ እንቅስቃሴ ሰላማዊ ለማድረግና ምልልሱን ለመጨመር ለባስ ብቻ ተብለው በተለዩ መስመሮች የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በአግባቡ እንዲጠቀሙ የሚመለከተው አካል ሁሉ ትብብር እንዲያደርግ በመግለፅ በቀጣይም የአገልግሎት መስመሩን ለመጨመር ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አሳውቋል።

በተመሳሳይ የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የትራፊክ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ጥናቶችን በባለሙያዎች በማስጠናትና በመለየት በትምህርት ቤቶች አከባቢ አስፈላጊ ምልክትና ማመለከቻ፣ የፍጥነት ወሰን መቀነሻና የእግረኛ መሻገሪያዎች በመስራት በትምህርት ቤቶች አደጋዎች እንዳይፈጠሩ የቅድመ መከላከል ስራዎች መሰረታቸው ተገልጿል።

ቢሮው ከትምህርት መከፈት ጋር ተያይዞ ሰላማዊ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዲኖር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር በጋራ በመሆን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የስምሪትና የቁጥጥር ስርአቱን ከጠናክሮ እንደሚሰራ ገልጿል።

በመጨረሻም ህብረተሰቡ በትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ቦታዎች ተማሪዎች ቅድሚያ እንዲያገኙ የተለመደው ትብብር እንዲደረግላቸው ቢሮው በአደራ ጭምር እያሳሰበ፤ 2015 መልካም የትምህርት ዘመን እንዲሆን መልካም ምኞቱን ገልጿል።

Leave a Reply