(ጥቅምት 5/2015 ዓ.ም አዲስ አበባ)፡- በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ከመደበኛ ስራዎቹ በተጓዳኝ በክረምት በጎ ፈቃድ መርሃ-ግብር ሰው ተኮር ስራዎች የአቅመ ደካሞች የቤት እድሰት የሁለት አባወራዎች ቤት ግንባታን በማጠናነቅ የርክክብ እና ምርቃት ፕሮግራም አደረገ።
ኤጀንሲው ከበጎ ፍቃደኛ ትራፊክ አስተናባሪዎችና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድት የሁለት አባወራዎችን ቤት ሙሉ ለሙሉ አፍርሶ በመስራት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ እና የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚደቅሳ ለባለቤቶቹ የቤቱን ቁልፍ አስረክበዋል።
በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ ባስተላለፉት መልዕክት ኤጀንሲው እና በጎ ፈቃደኛ የትራፊክ አስተናባሪ ወጣቶች ያከናወኑት የአቅማ ደካሞች ቤት እድሳት የሚደነቅ እና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ብለዋል።
አቶ ምትኩ ኤጀንሲው እና በጎ ፈቃደኛ የትራፊክ አስተናባሪ ወጣቶች የትራፊክ አደጋ እንዳይደርስ እና የጉዳቱን መጠን ለመቀነስ ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር በሀገራዊ እና በማህበራዊ ጉዳዮች አርአያ የሚሆን ስራ በመስራታቸው ሊመሰገኑ እንደሚገባ እና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚደቅሳ በቁልፍ ርክክብ ፕሮግራሙ ላይ ባስተላለፉት መልእክት ‘በመንገድ ትራፊክ ደህንነት ስራ የምንጊዜም የኤጀንሲያችን ሞደልና አርማ የሆናችሁ በጎ ፍቃደኛ ትራፊክ አስተናባሪ ወጣቶች እና በዚህ የህሊና እርካታን በሚሰጥ መልካም ተግባር የተሳተፋችሁ የኤጀንሲው አመራሮች እና ሰራተኞች እንዲሁም አጋር አካላት እንኳን ደስ አላችሁ አለን ብለዋል፡፡ ‘
ኤጀንሲው የከተማዋን የትራፊክ እንቅስቃሴ ሰላማዊና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ከመስራት ባሻገር በተለያዩ ሃገራዊና ከተማ አቀፍ በጎ ተግባራቶች ላይ ተሳትፎ ሲያደርግ መቆየቱን የጠቀሱት አቶ ክበበው በሁሉም የክረምት በጎ ፈቃድ ስራ የበጎ ፍቃደኛ የትራፊክ አስተናባሪ ወጣቶች ሚና የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
ቤቱ የታደሰላቸው አቅመ ደካማ አዛውንት ሲሳይ በዳኔ በበኩላቸው ‘ቤቱ ፈርሶ ከመታደሱ በፊት እላያችን ላይ ጣሪያው ተቀዶ ውሃ እየገባ ውስጡ ጭቃ ሆኖብን ልወድቅብን የነበረን ቤት ደርሳችሁልን ባመረ ቤት ውስጥ ስለገባሁ እግዚአብሄር ይመስገን፤ ለተደረገልኝ ነገር ፈጣሪ ብድሩን ይክፈላችሁ’ ብለዋል።
በኤጀንሲው እና በጎ ፈቃደኛ የትራፊክ አስተናባሪ ወጣቶች ሙሉ ለሙሉ ፈርሰው የተሰሩት የሁለቱ ቤቶች ግንባታ አንድ ሚሊየን ብር የፈጀ ሲሆን ሌሎች ስድስት ቤቶች ሁለት ሚሊየን ብር የሚገመት ዕድሳት ተደርጎላቸዋል።
በፕሮግራሙ ላይ የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ፣ የኤጀንሲው አመራሮች እና ሰራተኞች፣ የቅርንጫፍ ጽ/ቤት ስራ አስኪያጆች፣ በጎ ፈቃደኛ የትራፊክ አስተናባሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።