አዲስ አበባ፤ ህዳር 08፤ 2015፤ የትራንስፖርት ሠራተኞችን የመፈፀም አቅም ለማሳደግ ለማዕከል ዳይሬክተሮችና ባለሙያዎች ሲሰጥ የነበረው የሁለት ዙር ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡
ስልጠናው ቢሮው የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት ለመፈጸም፣ ተጨባጭ ውጤት የሚመጣበትን አሰራር ለመዘርጋትና መልካም ሥነ-ምግባር ያላቸው ሠራተኞችን ለማፍራት ትልቅ አቅም አለው፡፡
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የቴክኖሎጂ ዘርፉ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ወርቁ ደስታ የትራንስፖርት ቢሮ ባለሙያ ህዝባዊ ወገንተኝነት የተላበሰ እንዲሆን ለማስቻል የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናው የጎላ ሚና እንዳለው በመግለፅ የዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻል የዘርፉን ሙያዊ ስነ-ምግባር ጠብቆ አገልግሎት ለመስጠት ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል::
በስልጠናውም የጥቅም ግጭትን ምንነትና አስፈላጊነት እንዲሁም ስለሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳቶችን በውል በመረዳት ሰራተኞች የጎላ ሚና እንዲጫወቱ ያደርጋልም ተብሏል፡፡
ሙስናን ከመከላል አኳያ የሰራተኞችን ሚና ከማሳደግ ባሻገር፣ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማነት ከማረጋገጥ እና የሠራተኞችን መብት እና ግዴታ ለማሳወቅ መመሪያ ቁጥር 56/2010 ላይ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
በትራንስፖርት ዘርፉ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ፍፁም ሙያዊ ስነ ምግባር በመላበስ ለተሰማራበት ስራ ክብር ሰጥቶ ማገልገል እንዲችል እና ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመለየት የሚፈታበትን መንገድም በስልጠናው ተዳሷል፡፡
በሥልጠናው ሶስት መቶ (300) የሚሆኑ የተቋሙ ሰራተኞች በሁለት ዙር የተሳተፉ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ስልጠናው ለአስራ አንዱም የትራንስፖርት ቅርንጫፍ ሠራተኞች እየተሰጠ ይገኛል፡፡