የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ፤ ግንቦት 28/2016 ዓ.ም) ቢሮው በዘርፉ ያሉ ሴት አመራሮችን አቅም ለመገንባትና ለማሳደግ እንዲሁም በተሰማሩበት መስክ ውጤታማና ችግር ፈቺ ለማድረግ የአንድ ቀን የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጠ።
የትራንስፖርት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ወርቁ ደስታ ቢሮው በስሩ ያሉ ተጠሪ ተቋማትን ጭምር በማቀናጀትና በመምራት እንዲሁም ተመሳሳይ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን ገልፀው፤ በዋናነትም የሴት አመራሮችን የማስፈፀም አቅም እየገነባ እንደሚሄድ አሳውቀዋል።
ሥልጠናው በሶስት ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ሲሆን በዋናነት የሴቶችን አቅም መገንባትና ኢምፓወር ማድረግ እንዲሁም ስለ ሞተር አልባ ትራንስፖርትና ስለትራፊክ ደህንነት ምንነት ላይ ያተኮረ ነበር።
የቢሮው የትራንስፖርት ዘርፍ አቅም ግንባታ ዳይሬክተር አቶ ኃይለማርያም ተክለሚካኤል ስልጠናው ቀጣይነት እንደሚኖረውና ሴት አመራሮችን በክህሎትና በአመራርነት ያላቸውን ሚና ማሳደግ እንደሚገባ ገልፀዋል።
በስልጠናውም ከትራንስፖርት ቢሮ፣ ከቀላል ባቡር ፣ ከከተማ አውቶብስ ድርጅት ፣ ከአሽከርካሪ ተሸከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን፣ ከትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን የተውጣጡ ሴት ዳይሬክተሮችና ቡድን መሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።