(የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ መጋቢት 25/2016 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ በከተማዋ የሞተር ሳይክል ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አካላትን በአሰራርና በተደራጀ ሁኔታ ለመምራት የሞተር ሳይክል እና የኤሌክትሪክ ሞተር ሳይክል የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥን ለመወሰን አዲስ መመሪያ ቁጥር 155/2016 ተግባራዊ አድርጓል፡፡
በመመሪያውም ከአሽከርካሪው ውጪ ሌላ ሰው መጫን እንደማይቻልና ለእቃ ማመላለሻ ብቻ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ፣ ከኤሌክትሪክ ሞተር ሳይክል ውጪ አዲስ የአገልግሎት ፍቃድ እንደማይሰጥ፣ ከ250 አባላት ጀምሮ በማህበር በመደራጀት ፍቃድ እንደሚሰጥና አሁን በስራ ላይ የሚገኙ የሞተር ሳይክሎች በቀጣይ ቢሮው በሚያስቀምጠው የጊዜ ገደብ መነሻነት ወደ ኤሌክትሪክ የሞተር ሳይክል መለወጥ እንደሚገባ ቢሮው ያሳውቃል፡፡
ቢሮው ባወጣው መመሪያ መሰረት አገልግሎቱን የማይሰጡ ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች በመመሪያ ቁጥር 155/2016 መሰረት እንደ ጥፋቱ እርከን ቅጣት እንደሚጣልባቸው በጥብቅ ያሳስባል፡፡
ስለሆነም አዲሱ መመሪያ ወደ ተግባር እንዲገባ ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች እንዲሁም የሚመለከታችሁ ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ትብብር እንድታደርጉ ቢሮው ይጠይቃል፡፡