በመንገድ ደህንነት ችግር የሚከሰተው የሞት መጠን ባለፈው ዓመት 11.4 በመቶ መቀነሱን የአዲስ አበባ ከተማ የመንገድ ደህንነት ምክር ቤት አስታወቀ።

ምክር ቤቱ 3ኛ ዓመት መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ አካሂዷል።

የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊና የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ምትኩ አስማረ በጉባዔው መክፈቻ እንደተናገሩት የትራፊክ አደጋን በአንድ ተቋም ብቻ መቀነስ እንደማይቻል እና በከተማችን የሚታየው የትራፊክ እንቅስቃሴ በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት ከማድረሱ አስቀድሞ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል ።

ባለፈው ዓመት ለእይታ ጨለማ የሆኑ ቦታዎችን በመለየት መንገዶች የመብራት አምፓል በመትከል ፣ የመንገድ ጥገና በማድረግና የተሽከርካሪ ቁጥጥር በማድረግ አስከፊውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ በርካታ ተግባራትን ሲከውን ቆይቷል።

በዚህም የትራፊክ አደጋ ሞት ቁጥር በመቶ ሽህ ህዝብ በ2013 ዓመት 11ነጥብ 6 የነበረውን የትራፊክ አደጋ ምጣኔን በ11 ነጥብ 4 በመቶ መቀነስ መቻሉንም ገልፀዋል።

ባለፈው አንድ ዓመት በትራፊክ አደጋ በ411 ሰዎች የሞት እና በ1ሽህ 9 መቶ ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን በሪፖርቱ ተመላክቷል።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊና የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ምትኩ አስማረ ምክር ቤቱ የጀመራቸውን ስራዎች በማጠናከር የተመዘገቡ ውጤቶችን እንደመነሻ በመውሰድ ለላቀ ውጤት መስራት እንዳለበም አሳስበዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው ተበላሽተው የወደቁ ነባር የአደጋ ማስጠንቀቂያ መብራቶችን እና የእግረኛ መንገዶችን ፈጥኖ በመጠገን አንዲሁም የአደጋ መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂዎችን ጪምር በመጠቀም የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ጠይቀዋል።

በበዓል ወቅት በአስፓልት መንገድ ላይ የሚደረግን ግብይት ለማስቀረት ለከተማው ማህበረሰብ በስፋት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠት እዳለበትም የአዲስ አበባ ከተማ የመንገድ ደህንነት ምክር ቤት አሳስቧል።

የህዝብ ቁጥር እና በመንገድ ዳር የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መጨመር ለትራፊክ አደጋው መንስኤ መሆናቸውንም ተገልጿል።

Leave a Reply