በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎትን ሥርዓት ለማስያዝ በወጣው መመሪያ ዙሪያ በቦሌ ክፍለ ከተማ ከሚገኙ የባጃጅ ባለንብረቶች ጋር ውይይት ተካሄደ፡፡

በውይይቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ በከተማዋ የሚገኙ ባለሦስት እግር የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሸከርካሪዎች አሠራርን አስመልክቶ በቅርቡ ባወጣው መመሪያ ዙሪያ ገለፃ የተደረገ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ የቦሌ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋሲሁን ታረቀኝ የባለሦስት እግር የታክሲ አገልግሎት ሰጪ ተሸከርካሪዎች ሕጋዊ በሆነ መንገድ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ባለሥልጣኑ የአሠራር መመሪያ ማውጣቱን ተናግረዋል፡፡

በአዲሱ መመሪያ መሠረት የክልል ሰሌዳ ይዞ በአዲስ አበባ ከተማ የባጃጅ አገልግሎት መስጠት እንደማይቻል ያመለከቱት ሥራ አስኪያጁ፣ አንድ ማህበር እስከ 35 አባላት ድረስ ይዞ መደራጀት እንዳለበት በመመሪያው መቀመጡን በመጥቀስ የባጃጅ ባለንብረቶች ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናወን መመሪያውን አክበረው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ኮማንደር ብሥራት ታደለ በበኩላቸው የባለሦስት እግር የታክሲ አገልግሎት ሰጪ ተሸከርካሪዎች በተለይ መደበኛ ትራንስፖርት በማይደርስባቸው አካባቢዎች የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ጠቀሜታ ቢኖራቸውም በተጨባጭ ግን ሕጋዊነትን ያልተከተለ አካሄድ እና በወንጀል ተግባር ላይ ጭምር በመሠማራት በሰላምና ጸጥታ ላይ ችግር እንደሚፈጥሩ መስተዋሉን ገልጸዋል፡፡

አዲሱ መመሪያ ይህንነ ያልተገባ አካሄድ በማስተካከል ሕጋዊነትን ለማስፈን ወሳኝ በመሆኑ በጋራ ለተግባራዊነቱ መሥራት እንደሚያስፈልግም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ የክፍለ ከተማው የባለሦስት እግር ታክሲ ባለንብረቶች ሥራቸውን በሕጋዊ መንገድ ማከናወን እንዳለባቸው ያሳሰቡት የቦሌ ክፍለ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መርዕድ አስፋው፣ የውይይት መድረኩ በመመሪያው ዙሪያ ግንዛቤ በማስጨበጥ የተሳለጠ አሠራርን ለማስፈን መሠረት እንደሚጥል አመልክተዋል፡፡

@ቦሌ ኮሙኒኬሽን

Leave a Reply