የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የኮልፌ ቀራኒዮ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ከታክሲና የሀይገር ባስ ማህበራትና ባለንብረቶች ጋር የስራ ውል ስምምነት ሰነድ ተፈራረመ፡፡

ዛሬ በቀን 26/01/2015ዓ.ም የኮልፌ ቀራኒዩ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት በክፍለ ከተማው መሰብሰብያ አዳራሽ በቅርንጫፉ ስር የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙ የኮድ አንድ እና የሀይገር ባለንብረት ማህበር አመራሮችና ባለንብረቶች ጋር በቀጣይ በአገልግሎት አሰጣጡ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የጋራ ውይይት በማድረግ የስራ ውል ስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

የአዲስ አበባ የኮልፌ ቀራኒዮ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጀማል ሰፋ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን ፍትሀዊ ለማድረግና ባለው የትራንስፖርት አቅርቦት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችል በኮድ1 ታክሲና ሀይገር አውቶብስ የተማሪ ሰርቪስ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ አገልግሎት ሰጪዎች ለተማሪዎች አገልግሎቱን ከሰጡ በኃላ ጠዋት 1:30 ጀምሮ ከሰዓት ከ9:30 እሰከ 11:00 ባለው ጊዜ በተመደቡበት መስመር በመግባት ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡

ይህንን አሰራር ተፈጻሚ በማያደርጉ አገልግሎት ሰጪዎች ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ ኃላፊነት እንደማይወስድና ፍቃዱ ለመሰረዝ እንዲሁም በተቀመጠው መመሪያ መሰረት መስመር ባለመሸፈን እንደሚቀጣ ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩ የኮድ1 ታክሲና የሀይገር ማህበራት አመራሮችና ባለንብረቶች በአገልግሎት አሰጣጡ የሚገጥሞቸውን ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፤ በተለይ ከታለመለት ነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ እየገጠማቸው የሚገኙ ችግሮች መፈታት እንደሚገባቸው በጥያቄና በአስተያየት አንስተዋል፡፡

በመጨረሻም አገልግሎት አሰጣጡን የተሻለ ለማድረግ በተግዳሮት የተነሱ ችግሮችን በየደረጃው መፍትሄ እንደሚያኙ ገልፀው፤ አሁን የሚስተዋለውን የትራንስፖርት አቅርቦትና ፍላጎት ለመፍታት ያለንን የአገልግሎት አሰጣጥ አፈፃፀም በማሳደግና ማልደን በመነሳት እንዲሁም የተማሪ ወላጆችን ግንዛቤ በመፍጠር ተማሪዎቹን ወደ ትምህርት ገበታቸው በጠዋት በማድረስና ማታም በመመለስ ወደ መደበኛው የትራንስፖርት አገልግሎት መግባት እንደሚገባ ኃላፊው አበክረው ገልፀዋል፡፡

Leave a Reply