የትራንስፖርት ዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለፀ::

አዲስ አበባ፤ ህዳር 12፤ 2015 ዓ/ም፤ የትራንስፖርት ዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ዛሬ ከተጠሪ ተቋማት ጋር የ2015 በጀት ዓመት የ አራት ወር የስራ እቅድ አፈፃፀም ሪፖርቱን በገመገመበት ወቅት ገለፀ።

ቢሮው በአራት ወራቱ በእቅድ ተይዘው የተከናወኑ ተግባራትንና እቅድ አፈጻጸማቸውን የገመገመ ሲሆን፤ በሪፖርቱም በዘርፉ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የተሰሩ ስራዎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል የተገልጋዩን እርካታ ማሳደግና ብልሹ አሰራርን በመታገል የተጠያቂነት ስርዓት በመዘርጋት ትኩረት ተሰጥቷ ሲሰራ እንደነበር ተገልፆል፡፡

በተመሳሳይ የከተማዋን የትራፊክ እንቅስቃሴን ሰላማዊ ለማድረግ፣ የትራፊክ ደንብ ተላላፊዎች ባሉበት ቦታ ሆነው ክፍያ እንዲፈፅሙ መደረጉ፣ ለአውቶብስ ብቻ የተለዩ መስመሮችን ቁጥጥር በማድረግ የታለመላቸውን አገልግሎት እንዲሰጡ ከማድረግ አኳያ ውጤት የሚያመጡ ስራዎች መሰራታቸውና የወጡ ደንቦችን የማስተግበርና የክትትል ስራ መሰራቱ እንዲሁም የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ጋር በተያያዘ ሞዴል ተቋማትን መፍጠር መቻሉ፣ የአገልግሎት መስኮቶች ለቪ አይ ፒ፣ ለዲያስፖራዎች፤ ለዶክተሮች፤ ለሀገር መከላከያዎች መከፈታቸው የተገልጋዩን እርካታ መጨመሩ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም በብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በአንበሳና ሸገር የብዙሀን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት የቀን ምልልስን በመጨመርና ዘርፉን በቴክኖሎጂ ለማሳደግ ዘመናዊ ሶፍትዌር መልማቱ ተገልፆል፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ ዘርፉን በቴክኖሎጂ በመደገፍ አገልግሎት አሰጣጡን የተሻለ ለማድረግ መስራት እንደሚገባና በዘርፉ የሚሰጡ አገልግሎቶችንን ከሰው ንክኪ የፀዳ ማድረግ፣ የመንጃ ፍቃድ ማሰልጠኛና የተሸከርካሪ ምርመራ ተቋማት ክትትልና ድጋፍ መጠናከር ይገባዋል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም ቢሮው በስሩ ላሉ የስምሪትና ቁጥጥር ባለሙያዎች ሙያዊ ስነምግባርን ተላብሰው አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ተከታታይነት ያላቸው የአቅም ግንበታ ስልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን በመግለፅ ፤ ዘርፉን በጋራ ለማሳደግና ለማዘመን በተጠሪ ተቋማቱ በአራት ወራት የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራትና ቅንጅታዊ አሰራሮች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው በአንክሮ ገልፀዋል፡፡

Leave a Reply