አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 27፤ 2015 ዓ.ም፤ ባሳለፍናቸው ስድስት ወራት ከአገልግሎት ክፍያ ከ1.4 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ዛሬ በተቋሙ የመሰብሰብያ አዳራሽ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አሳውቋል፡፡
የባስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መስፍን መንግስቱ እንደተናገሩት በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ውስጥ 665 ሺህ 742 ተገልጋዮችን ማስተናገዳቸውን ጠቁመው በአገል-ግሎት ክፍያውም 1 ቢሊየን 450 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገልፀዋል፡፡
ዋና ስራ አስኪያጁ አያይዘውም በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በዋናነት የአሽከርካሪና የተሽከርካሪ አገልግሎቶች እንደሚሰጡ በመግለፅ ለስድስት ወራት ለማከናወን በእቅድ ተያዘው አኳያ አንድ መቶ አስራ አራት ከመቶ መፈፀሙን አስረድተው፤ በአሽከርካሪ ዘርፍ 100,662 የመንጃ ፍቃድ እድሳት መደረጉ፣ ለ31,913 እጩ አሽከርካሪዎች አዲስ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ወይም መንጃ ፍቃድ መስጠት ተችሏል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ በተሽከርካሪ ዘርፍ ለ424,590 ተገልጋዮች በሁሉም ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት አገልግሎቱን መስጠት የተቻለ ሲሆን፤ ለ18,538 አዲስ ተሽከርካሪዎች ምዝገባና ለ11,210 ተሸከርካሪዎች ላይ ድንገተኛ ምርመራ በማድረግ በቴክኒክ ብቃታቸው ብቁ የሆኑትንና ያልሆኑትም በመለየት ብቁ ያሆኑት የተሸከርካሪው ጉድለት እንዲስተካከል መደረጉን ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም መቻሉና የሰራተኞች የአገልጋይነት መንፈስ እየጨመረ በመምጣቱ በበጀት ዓመቱ በስድስት ወራት አበረታች ውጤቶች መመዝገብ መቻሉን በመግለፅ፤ ህብረተሰቡ በተቋሙ የሚሰጡ አገልግሎትን ለማግኘት አስፈላጊውን መረጃ ብቻ አሟልቶ በመገኘት ከህገ ወጥ ጉዳይ አስፈጻሚዎች እንዳይጋለጡ የአሽከርካሪ ተሸከርካሪና ፍቃድ ቁጥጥር ባለስልጣ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መስፍን መንግስቱ አሳስበዋል፡፡
ዘገባው:-የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ነው