በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድና ትራንስፖርት ዘርፍን ለመምራት የተሾሙ አመራሮች ከነባር አመራሮች ጋር በከተማዋ መንገዶች ባለስልጣን ዋና መስሪያ ቤት የትውውቅ ፕሮግራም አካሂደዋል፡፡
በትውውቅ ፕሮግራሙ ላይም የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ኢንጂነር ሰለሞን ኪዳኔ በቀጣይ ሁለት ዓመታት የከተማዋን ትራንስፖርት ለማሻሻል በዋናነት መሰራት ስላለባቸው ጉዳዮች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ምክትል ከንቲባው የመንገድና ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል አመራሮች ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የአዲስ አበባን የትራንስፖርት ስርዓት ለማዘመን የትራንስፖርት መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋት አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ከንቲባው ሰፋፊ እና ረጃጅም መንገዶችን፣ ተርሚናል፣ ዴፖ፣ ሼዶችን መገንባትና ማስፋፋት ላይ ትኩረት ሰጥተን መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ አንድ አውቶቡስ ለ3,330 ሰው እንደሚቀርብ የተናገሩት ምክትል ከንቲባው የትራንስፖርት ፍላጎትና አቅርቦትን ለማመጣጠን መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ጤነኛ አሽከርካሪና ተሸከርካሪ በትራፊክ ፍሰቱ ውስጥ እንዲኖር በማድረግ መዲናችንን ከአደጋ ነጻ የሆነች እንድትሆን በቀጣዮቹ ዓመታት መስራት ይገባናል ብለዋል፡፡
እንደ ምክትል ከንቲባው ገለጻ የመዲናዋን መንገድና ትራንስፖርት ስርዓት አስተማማኝ ማድረግ ከአዲሱ አመራር እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡
የትራንስፖርት ተጠቃሚው ህብረተሰብ በከተማዋ ትራንስፖርት አገልግሎት እምነት እንዲኖረው ተጠቃሚዎችን በሚፈልጉት ሰዓት ካሰቡበት ቦታ እንዲደርሱ ለማድረግ መስራት ይገባናል ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ሁሉም ሰው ከፍሎ መጓዝ የሚችልበት የትራንስፖርት ስርዓት ሊኖረን ይገባል ያሉት ምክትል ከንቲባው ለዚህም ለአገልግሎቱ የሚመጥን ዋጋ ማቅረብ አለብን ብለዋል፡፡
ሌላ ትኩረት ሰጥተን መስራት ያለብን የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ምቹ ማድረግ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የመንገድና ትራንስፖርት ዘርፉን በእውቀት ለመምራት እንዲቻልም የአቅም ማጎልበቻ ስራዎች ላይም ይሰራል ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ የመንገድና ትራንስፖርት ዘርፉን ለአፍሪካም ጭምር ተሞክሮ በሚሆን ደረጃ ማሳደግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
በመንገድና ትራንስፖርት ዘርፍ አዲስ የተሾሙ የሥራ ኃላፊዎችም ኢ/ር ሞገስ ጥበቡ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር፣ አቶ ምትኩ አስማረ የአዲስ አበባ ከተማ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ታከለ ሉሌና የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የመንገድ መሰረተ ልማት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ፣ ኢ/ር ሰመረ ጅላሉ የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ፣ አቶ አስመላሽ ኪዳነማሪያም የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ፈንድ ጽ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ፣ ወ/ሮ ሀዋ ዋቢ የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ፈንድ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ናቸው፡፡