ቢሮው የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀሙን ገመገመ።

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ የ2015 የዘጠኝ ወር እቅድ አፈፃፀሙን ከማዕከልና ቅርንጫፍ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር በጋራ ገምግሟል፡፡

በእለቱም የቢሮው እቅድና በጀት ዳይሬክተር አቶ ይታያል ደጀኔ የቢሮውን የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን፤ በቀረበው ሪፖርት ላይም ውይይት ተደርጓል።

በሪፖርቱም በእቅድ ተይዘው የተከናወኑ ተግባራትንና እቅድ አፈጻጸማቸውን የተገመገመ ሲሆን፤ በዘርፉ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የተሰሩ ስራዎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል የተገልጋዩን እርካታ ለማሳደግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች፣ ብልሹ አሰራርን በመታገል የተጠያቂነት ስርዓት በመዘርጋት ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ እንደነበር ተገልፆል፡፡

በዋናነትም በአማካይ በየቀኑ 10,435 ተሽከርካሪዎች ማሰማራት መቻሉን፣ ባለው የአቅርቦት መጠን በቀን 3.1 ሚሊየን ጉዞ መፈጠር መቻሉንና ስምሪትና ቁጥጥር ስርዓቱን በማጠናከር በ50 ሺ 233 አጥፊ አሽከርካሪዎች እርምጃ መወሰዱን በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ምክትል ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ዳዊት ዘለቀ በዘርፉ የሚሰጠውን አገልግሎት የተሻለ ለማድረግ በዘጠኝ ወሩ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆኑን በመግለፅ፤ ዘርፉን በቴክኖሎጂ በማዘመን የከተማዋን እድገት የሚመጥን የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን በማንሳት ለውጥ በማምጣጥ በትኩረት መሰራት እንደሚገባ በአንክሮ ገልፀው፤ በእቅድ ተይዘው ያልተተገበሩትን በመለየት በቀሪ ሶስት ወራት ውስጥ መተግበር እንደሚገባና የስምሪትና ቁጥጥር ስራውን በማጠናከር ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

ተወያዮችም በቢሮው በዘጠኝ ወራት የተሰሩ በርካታ አበረታች ስራዎች መኖራቸውን ገልፀው፤ በቀጣይ ቢሮው ሊፈታቸውና ትኩረት ሊሰጥባቸው ይገባል ያሉትን በተለይ ከአገልግሎት አሰጣጡ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዋናነትም ከታሪፍ በላይ ማስከፈልና ማቆራረጥን አንስተው ቢሮው አገልግሎት አሰጣጡን ከማንዋል አሰራር ወደ ቴክኖሎጂ ሊሻገር እንደሚገባ በእቅድ አፈጻጸም ውይይቱ ወቅት ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀብተወልድ ሸዋንግዛው በበጀት አመቱ ቢሮውን በአዲስ መልክ በማደራጀትና የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ስራዎች በጋራ መሰራት መቻላቸው ውጤታማ እንድንሆን ማስቻሉንና በተወያዮች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

Leave a Reply