በትራፊክ አደጋ የሞት መጠን መቀነሱ  ተገለጸ

በትራፊክ አደጋ የሞት መጠን መቀነሱ ተገለጸ

ካለፈው ዓመት የዘጠኝ ወር ሪፖርት ጋር ሲነጻጸር የትራፊክ አደጋ የሞት መጠን በቁጥር 711 ወይም  17.7% መቀነሱ  በብሔራዊ መንገድ ደህንነት ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ አስታወቀ፡፡

መደበኛ ጉባኤውን የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ የመክፈቻ ንግግር በማድረግ ያስጀመሩ ሲሆን በንግግራቸውም በበጀት ዓመቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመንገድ ደህንነት ተግባራትን ትኩረት በመስጠት ሲያከናውን እንደነበረ በመጥቀስ የአሰራር ስርዓቶችን  የማሻሻል፣ ሀገር አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን የማካሄድ እንዲሁም የተቀናጀ የቁጥጥርና የህግ ማስከበር ስራዎች በዋናነት በማከናወን የተወሰነ ለውጥ ማምጣት ቢቻልም በአሁን ወቅት በኮሮና ቫይረስ ከተመዘገበው የሞት መጠን በላይ በትራፊክ አደጋ ያጣነው እንደሚበልጥ በመግለጽ የትራፊክ አደጋውን ለመቀነስ በመንገድ ደህንነት የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ በቅንጅት ለመስራት በተከናወኑ ተግባራት ላይ ለተሳተፉ ባለድርሻ አካላትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በጉባኤው የብሔራዊ መንገድ ደህንነት ምክር ቤት ጽ/ቤት ፣የመሰረተ ልማት፣የቁጥጥርና ህግ ማስከበር ፣የትምህርትና ግንዛቤ፣የአፋጣኝ ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ንኡሳን ኮሚቴዎች እንዲሁም የክልል ትራንስፖርት ቢሮዎች በበጀት ዓመቱ ያከናወኗቸውን ተግባራት አቅርበዋል፡፡

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ከግንዛቤ ማስጨበጥ አንጻር ከጳጉሜን ወር ጀምሮ “እንደርሳለን” በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የመንገድ ደህንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች በማዘጋጀት መልካም ስነምግባር ያላቸውን አሽከርካሪዎች የማበረታታት፣የመንገድ ደህንነት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ በህዝብ ተወካዮች አባላት  እና በህብረተሰቡ ዘንድ ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት እንዲሁም በተለያዩ የተግባቦት መሳሪያዎችን በመጠቀም የግንዛቤ ማስጨበት ስራዎች መከናወናቸው ተነስተዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ዘለቄታዊ የሆኑ ግንዛቤዎችን ለማሳደግ በትምህርት ሚኒስቴር የመንገድ ደህንነትን በስርዓተ ትምህርት ውስጥ ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ስርዓት ውስጥ እንዲሁም በጎልማሶችና መደበኛ ባልሆኑ የትምህርት የመማሪያ ስርዓቶች ውስጥ እንዲካተት መደረጉን ተገልጿል፡፡በተጨማሪም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም በሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም እንዲካተት ስራዎች መጀመራቸው ተገልጿል፡፡

ደህንነታቸው የተጠበቁ የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ከመተግበር አንጻር የአሰራር ስርዓቶችን የማሻሻል፣ የመንገድ ላይ የምልክትና ቀለም የማስተካከል ፣የአደጋ መከላከያ የመንገድ ብረቶች ጥገና እንዲሁም የክፍያ መንገዶች ላይ የክትትልና የቁጥጥር ስራዎች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን የመሰረተ ልማት ንኡስ ኮሚቴው አንስተዋል፡፡

የመንገድ ደህንነት የህግ ማስከበርና የቁጥጥር ስራዎችን ከማጠናከር አንጻርም የተሽከርካሪ ደህንነትን ለማስጠበቅ በተሽከርካሪ የደህንነት ቀበቶ መመሪያ ተግባራዊ የማድረግ፣የትራፊክ የቅጣት ክፍያ ስርዓትን ተደራሽ የማድረግ እና የቴክኖሎጂ የአሰራር ስርዓቶችን የማሻሻልና የተቀናጀ የቁጥጥር ስርዓትን በፌደራል፣ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በማጠናከር በበጀት ዓመቱ መከናወናቸውን የህግ ማስከበርና ቁጥጥር ንኡስ ኮሚቴ የገለጸ ሲሆን ሶስተኛ ወገን ኢንሹራንስ ተጠቃሚዎች መሻሻሉን፣የደህንነት ቀበቶ አጠቃቀም እና ቅንጅታዊ አሰራሮች ዙሪያ የተሻለ ውጤቶች መታየታቸውና የለሊት ጉዞ ፍሰት መቀነሳቸው ተነስቷል፡፡

የድንገተኛ እና የአፋጣኝ ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ከማጠናከር አንጻር የአቅም ግንባታ ስራዎች ፣የድንገተኛ አገልግሎት የሚሰጡ አምቡላንሶች ግዥ እና ስርጭት፣ የድንገተኛ እና ጽኑ ህሙማን አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የማሳደግ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን የተቀናጀ የጥሪ ማእከል አሰራር ለመዘርጋት በሂደት ላይ መሆኑን ተገልጿል፡፡

በጉባኤው በGTP II የተቀመጠውን ግብ ለማሳካትና የሞት መጠንን ለመቀነስ በመንገድ ደህንነት ዙሪያ በቅንጅት ለመስራት የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸው ክብርት ሚኒስቴር ወ/ሮ ዳግማዊት አሳስበዋል፡፡

@ብሔራዊ መንገድ ደህንነት ምክር ቤት ጽ/ቤት

Leave a Reply