[:en]
የአለም ኤድስ ቀን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ እና የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሰራተኞች ደም ለገሱ፡፡
“ለኤች አይቪ ኤድስ ይበልጥ ተጋላጭ ነን፤ እንመርመር፤ እራሳችንን እንወቅ” በሚል መሪ ቃል የሚከበረው 30ኛውን አገር አቀፍ የኤድስ ቀን ምክንያት በማድረግ ዛሬ በመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ በተካሄደው ፕሮግራም በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪ ዶ/ር ኢ/ር ሰሎሞን ኪዳኔ ደም ለግሰዋል፡፡
ሌሎች አመራሮችና ሰራተኞችም እንዲዚሁ ደም በመለገስ የዜጎች ሕይወትን የመታዳግ በጎ ፈቃደኝነታቸውን አሳይተዋል፡፡
የአለም የኤድስ ቀን ምክንያት በማድረግ በተካሄደው ፕሮግራም የተሳተፉ አመራሮችና ሰራተኞች በሰጡት አስተያየት ራሳቸውን ከኤች አይ ቪ/ ኤድስ በመከላከል የቤተሰቦቻቸውንና የህብረተሰቡን ደህንነት እንዲጠበቅ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡
አያይዘውም ለወገኖች የሚደረገው የደም ልገሳ የዜጎችን ህይወት የሚታደግ በመሆኑ ውስጣዊ እርካታን የፈጠረላቸው እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ደም ልገሳ የራስን ጤና መጠበቂያ ሰብአዊ ተግባር ከመሆኑም በተጨማሪ በጎነትን ማስተማር የሚቻልበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በራስ ፈቃድና ተነሳሽነት ደም መለገስ ከደም እጦት ጋር ለሚቀርቡ ጥያቄዎቸ አፋጣኝ ምላሽ የሚፈልግ መሆኑን ጠቁመው አንድም ዜጋ በደም እጦት ምክንያት እንዳይሞት በበጎ ፍቃድ ደም የመለገስ ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጠሉ ቃል ግብተዋል፡፡
በደም ባንክ አገልግሎት የደም ለጋሾች አስተባባሪ አቶ መላኩ አሰበ በበኩላቸው በአገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ የደም ባንኮች ከበጎ ፍቃድ ደም ለጋሾች የተሰበሰበውን ለተጠቃሚው ማህበረሰብ በነጻ ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በዚህም የእናቶችንና የህጻናትን ሞት እንዲሁም በድንገተኛ አደጋ ጊዜ የሚከሰትን ህይወት መጥፋት መቀነስ መቻሉንም አስረድተዋል፡፡
ከለጋሾች የሚሰበሰበው ደም በሀገሪቱ ካለው የህዝብ ብዛት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመው መሰብሰብ ካለበት 300 ሺህ ዩኒት የደም ከረጢት እየተሰበሰበ ያለው ከ105 ሺህ ዩኒት የደም ከረጢት በታች መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ሁሉም ማህበረስብ ደም በመለገስ ሰብአዊ ግዴታውን በመወጣት በደም እጦት ምክንያት የሚከሰት ሞትን መቀነስ እንደሚገባ አስተባባሪው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘገባው፦ በትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነው
ለበለጠ መረጃ፦ 011 557 32 66