ለአዲስ አበባ ፈጣን አውቶቡስ መንገድ ግንባታ የሚውል የብድር ስምምነት ተፈረመ

ለአዲስ አበባ ፈጣን አውቶቡስ መንገድ ግንባታ የሚውል የብድር ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2012፤ በኢትዮጵያና በኮሪያ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ መካከል ለአዲስ አበባ ከተማ ፈጣን የከተማ አውቶቡስ B6 ኮሪደር ፕሮጀክት የሚውል የ63 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የብድር ስምምነት ተፈርሟል።

የብድር ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ እና የኮሪያ ኤግዚም ባንክ ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚ ሺን ዲኦግ-ዮንግ በዓለም ጤና ድርጅት የተቀመጠውን ርቀትን የመጠበቅ ፕሮቶኮል መሠረት በማድረግ ተፈራርመዋል።

B6 ፈጣን የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ስራ ሲጀምር የመዲናዋን ነዋሪዎች ዘመናዊ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ለማስፋፋት እገዛ እንደሚኖረው ተብራርቷል፡፡

ብድሩ በ40 ዓመት የሚከፈል ሲሆን 15 ዓመት የእፎይታ ጊዜ ይኖረዋል፡፡ የወለድ መጠኑም 0.01 በመቶ እንደሆነ በፊርማ ስነ ስርዓቱ ወቅት ተገልጿል።

B6 ፈጣን የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት 11.05 ኪ.ሜትር ርዝመት የሚኖረው ሲሆን ከመነሻው እስከ መድረሻው በአማካኝ በ630 ሜትር ርቀት 17 የአውቶቡስ ፌርማታና ሁለት ተርሚናል እንደሚኖሩት ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ B6 ኮሪደር ከጦር ኃይሎች አደባባይ ተነስቶ በካርል አደባባይ ፑሽኪን አደባባይን በመሻገር ጎተራን አቋርጦ ወሎ ሰፈርን አልፎ መዳረሻው ቦሌ ኤርፖርት እንደሚሆን ታውቋል፡፡

Leave a Reply