================================================
(ትራንስፖርት ቢሮ፣ ሐምሌ 13/ 2016 ዓ.ም)
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የ2016 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀሙን ከአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን፣ ከትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን፣ ከቀላል ባቡርና ከከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ጋር በጋራ ገምግሟል፡፡
በእለቱም የቢሮውና የተጠሪ ተቋማት የ2016 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርትና የ2017 እቅድ ያቀረቡ ሲሆን፤ በቀረበው ሪፖርት ላይም ውይይት ተደርጓል።
በሪፖርቱም በእቅድ ተይዘው የተከናወኑ ተግባራትን ከእቅዳቸው አንጻር አፈጻጸማቸው የተገመገመ ሲሆን፤ በዋናነትም በሪፖርቱ የብዙሀን ትራንስፖርት አቅርቦትን የማሳደግ፣ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ብቃት የማረጋገጥና ስራ የመስራት፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊ አገልግሎት ምሳ ሰዓትን ጨምሮ ህብረተሰቡን የሚያረካ አገልግሎት የመስጠት፣ የትራፊክ ደህንነትን ማረጋገጥና የትራፊክ ፍሰትን የማሻሻል ስራ መሰራቱ ተጠቁሟል።
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ያብባል አዲስ
የዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ የተሻለ ለማድረግ እቅድ አቅዶ በትኩረት መስራት እንደሚገባና በዘርፉ የግል ባለሀብቱን ማሳተፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
ኃላፊው አክለውም የህዝብ ትራንስፖርት አቅርቦትን ማሳደግ፣ ዘርፉን በቴክኖሎጂ ማዘመን፣ በመንገድ ደህንነትና ፍሰት ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ በአንክሮ ገልፀዋል።
በመጨረሻም ቢሮውና ተጠሪ ተቋማቱ በሌብነትና ብልሹ አሰራር ጋር ተያይዞ የቅድመ መከላከል ስራዎች ላይ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት እንደሚሻና የኮሙኒኬሽንና የሚዲያ ተግባራትን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።