የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ህብረተሰቡን የማንቃት ስራ ተከታታይነት ባለው መልኩ እንደሚሰራ የትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የትራንስፖርት ቢሮ ከኮከብ ሚዲያና ማስታወቂያ ጋር በመተባበር በመዲናዋ ለሁለት ቀናት የጎዳና ላይ ቅስቀሳ አካሂዷል፡፡
በቅስቀሳው ማስጀመሪያ ወቅት የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ስጦታው አካለ እንደተናገሩት በህብረተሰቡ ዘንድ የሚታየውን መዘናጋት ለማስቀረት የማንቃት ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የቢሮው ኃላፊ አያይዘውም ህብረተሰቡ በኮሮና ቫይረስ ጥርጣሬ ሲኖረው ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ምርመራ እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ በመምጣቱ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡
ነዋሪዎች አክለውም በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች የቫይረሱ ስርጭት በቁጥርና በፍጥነት በመጨመር አሳሳቢ ደረጃ መድረሱንም ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ነዋሪዎች ስርጭቱን ለመቀነስ በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
የትራንስፖርት ቢሮ ከግንቦት 17 እና 18 ቀን 2012 ዓ.ም ታዋቂ አርቲስቶችን በማሳተፍ በከተማዋ አስሩም ክፍለ ከተሞች ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ሰርቷል፡፡