አዲስ አበባ፣ የካቲት 14 ቀን 2016 ዓ.ም፡- በከተማዋ የመጀመሪያው የብልህ ትራንስፖርት የትራፊክ ቁጥጥር ስርዓት ተግባራዊ የሚደረግበት የኢንግሊዝ ኤምባሲ – 22 – ቦሌ ኤድናሞል የመንገድ ግንባታ ስራ ተጀምሯል፡፡
የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ የአማካሪ ድርጅት ተጠሪ መሐንዲስ ኢንጅነር ታከለ አብርሃም እንደገለፁት፤ በአሁኑ ወቅት የመንገድ ፕሮጀክቱ መነሻ አካባቢ የአፈር ቆረጣ እና የድሬኔጅ መስመሮችን ለመዘርጋት የሚያስችሉ የቁፋሮ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
ተጠሪ መሃንዲሱ አክለውም ይህ በዓይነቱ ለየት ያለው እና ዘመናዊ የትራፊክ የቁጥጥር ስርዓት ተግባራዊ የሚደረግበት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አካል ጉዳተኞችን እና እግረኞችን በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ የሚያደርግ ይሆናልም ብለዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ አደጋዎችን የሚቀንሱና የትራፊክ ፍሰቱን የሚያሻሽሉ ልዩ ልዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በአደባባዮችና በመንገድ መጋጠሚያዎች ላይ ተግባራዊ እንደሚደረጉ ኢንጂነር ታከለ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በተለያዩ የመንገድ መጋጠሚያዎች ላይ ተተክለው ስራ ሲጀምሩ የከተማዋን የትራፊክ ቁጥጥር ስርዓት በአንድ ማዕከል ለመቆጣጠር ያስችላል።
ይህን የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት የቻይናው ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚያከናውነው ሲሆን የማማከርና የቁጥጥር ስራውን ደግሞ የጀርመኑ ሬል ዌይ ኢንጅነርስ አማካሪ ድርጅት የሚከታተለው ይሆናል፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቱ ካለው አጠቃላይ 4.4 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 25 ሜትር የጎን ስፋት በተጨማሪ 4 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው በርካታ የመንገድ መጋጠሚያዎችም የግንባታው አካል ይሆናሉ፡፡
በሌላ በኩል የመንገድ ፕሮጀክቱ ዲዛይን እንደየ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ዘመናዊ የእግረኛ መንገዶች፣ የታክሲ መጫኛና ማውረጃ ቦታዎች፣ የመዝናኛ ቦታዎችንና ሌሎችንም አገልግሎቶች የተካተቱበት ነው፡፡