የአዲስ አበባ ፈጣን የትራንዚት አውቶቡስ አገልግሎት ከሦስት ዓመት በኋላ ይጀመራል ተባለ 157 አውቶቡሶች ለሚሠማሩበት የመጀመርያው ምዕራፍ 130 ሚሊዮን ዩሮ ተመድቧል፡፡

የአዲስ አበባ ፈጣን የትራንዚት አውቶቡስ አገልግሎት ከሦስት ዓመት በኋላ ይጀመራል ተባለ 157 አውቶቡሶች ለሚሠማሩበት የመጀመርያው ምዕራፍ 130 ሚሊዮን ዩሮ ተመድቧል፡፡

[:en]

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን የብዙኃን ትራንስፖርት አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ ያስቻላል ያለውን የፈጣን ትራንዚት አውቶቡስ (ቢአርቲ-ቢ2 ኮሪደር) አገልግሎት፣ በሦስት ዓመታት ውስጥ ሥራ ለማስጀመር እየሠራ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡

ከፈረንሣይ የልማት ትብብር ኤጀንሲ በተገኘ 85 ሚሊዮን ዩሮ ብድርና ዕርዳታ፣ እንዲሁም በከተማው አስተዳደር በሚሸፈን 45 ሚሊዮን ዩሮ በጠቅላላው በ130 ሚሊዮን ዩሮ በጀት ግንባታው እንደሚካሄድ ለሪፖርተር የገለጹት፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ፕሮግራም ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት የቢአርቲ ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ፀጋዬ (ኢንጂነር) ናቸው፡፡ የፈጣን ትራንዚት አውቶቡስ ፕሮጀክት አገልግሎት ከዊንጌት እስከ ጀሞ መንደር የሚያገናኝ የ17.3 ኪሎ ሜትር ዝርመት ያለው የትራንስፖርት ኮሪደር እንደሆነ አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል፡፡

በመጀመርያው የፈጣን ትራንዚት አውቶቡስ ትራንስፖርት ኮሪደር 157 አውቶቡሶች እንደሚሰማሩ ተጠቅሷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱን ዝርዝር ዲዛይን በሦስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሠራ እንደሚገኝም ታውቋል፡፡ ከዝርዝር ዲዛይን ሥራው ጎን ለጎን የግንባታ ተቋራጭ ለመቅጠር፣ ብሎም የአውቶቡሶች ግዥና የስማርት ሲስተም ግዥዎችን ለማካሄድ ጨረታ እንደሚወጣ አቶ ቴዎድሮስ አስታውቀዋል፡፡ አራት መሠረታዊ የግዥ ሥራዎች የሚከናወኑበት የጨረታ ሒደትም በመጪዎቹ አሥር ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተጠቁሟል፡፡

ከዊንጌት በፓስተር አድርጎ አውቶቡስ ተራን አቋርጦ በተክለ ሃይማኖት በኩል ሜክሲኮን ይዞ በቄራ ወደ ጆሞ መንደር የሚዘረጋውና 23 ጣቢያዎችን የሚያካትተው ይህ ፕሮጀክት፣ እንደ ቀላል ባቡር ፕሮጀክቱ ሁሉ በመንገድ መሀል ለመሀል የሚዘረጋ ነው፡፡ 40 በመቶ የከተማዋ ነዋሪዎች የሚገኙባቸውን አምስት ክፍላተ ከተሞች የሚያካልለው ይህ የአውቶቡስ መስመር፣ በአንድ ሰዓትና በአንድ አቅጣጫ ብቻ 6,500 ተሳፋሪዎችን የማመላለስ አቅም እንዳለውም ለመረዳት ተችሏል፡፡

በሰባት ሜትር የመንገድ ስፋት በሁለት አቅጣጫ የሚገነባው ይህ የአውቶቡስ መስመር፣ አምስት አገልግሎቶችን በመስጠት ይጀምራል ተብሏል፡፡ ይኼውም ከመነሻ እስከ መድረሻ ለሚጓዙ፣ ፈጣን የኤክስፕረስ ተሳፋሪዎች፣ ወደ ሌሎች መንገዶች በመግባት የሚሰጡትን ጨምሮ ሌሎችም አገልግሎቶችን በኤሌክትሮኒክ ካርድ የታገዘ የብዙኃን አገልግሎት እንደሚያቀርብ ይጠበቃል፡፡ 18 ሜትርና 12 ሜትር ዝርመት ያላቸው አውቶቡሶች ለአገልግሎቱ እንደሚቀርቡ የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፣ አውቶቡሶቹ ከውጭ ተገዝተው ይገቡ ወይም በአገር ውስጥ ይገጣጠሙ እንደሆነ ተጠይቀው ይህንን የሚወስነው የከተማው አስተዳደር እንደሆነ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የፕሮጀክቱ የዲዛይን አማካሪ የሆነው የፈረንሣዩ ሳፌጅ ኩባንያ ከሁለት ዓመት በፊት ከአገር በቀልና ከእንግሊዝ ሸሪኮቹ ጋር በመሆን፣ ከአዲስ አበባ ከተማ መንዶች ባለሥልጣን ጋር የ67 ሚሊዮን ብር ስምምነት ተፈራርሞ ነበር፡፡ ኩባንያው ከዲዛይን ማማከር ባሻገር የግንባታ ቁጥጥር ሥራም ያከናውናል፡፡ ሆኖም ኩባንያው በወቅቱ ወደ አገር ውስጥ ገብቶና ፈቃድ አውጥ ሥራ ለመጀመር ጊዜ በመፍጀቱ፣ የፕሮጀክቱን ሒደት እንዳጓተተው አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት በተደረገው ስምምነት መሠረት ከሆነ፣ በዚህ ዓመት አጋማሽ የፕሮጀክቱ ግንባታ መጠናቀቅ ይጠበቅበት ነበር፡፡ ይሁንና የዲዛይን ክለሳና የዝርዝር ዲዛይን ሥራውን ማሻሻል በማስፈለጉ ሳቢያ፣ ፕሮጀክቱ ከታሰበው ጊዜ ሊዘገይ መቻሉ ታውቋል፡፡ የፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራዎች በሁለት ዓመታት ውስጥ ሊጠናቀቁ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡

እንዲህ ያለው የፈጣን ትራንዚት አውቶቡስ አገልግሎት እንደ ታንዛንያ ባሉ የአፍሪካ አገሮች መተግበር ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ታንዛንያ ከዓለም ባንክ ባገኘችው የገንዘብ ድጋፍ የ140 ያህል አውቶቡሶችን ያሰማራችበት የፈጣን ትራንዚት አውቶቡስ አገልግሎት፣ የዲዛይንና ተያያዥ ችግሮች አጋጥመውታል፡፡ በጎርፍ በተጥለቀለቀው የአውቶቡሶቹ መናኸሪያ ሳቢያ 79 ያህል አውቶቡሶች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮች በአዲስ አበባ ፕሮጀክት እንዳያጋጥሙ ጥናቶች በሚገባ መካሄዳቸውንና ከታንዛንያው የፈጣን ትራንዚት አውቶቡስ ፕሮጀክት ጠቃሚ ተሞክሮዎች መወሰዳቸውን አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል፡፡ የታንዛንያ ፈጣን ትራንዚት አውቶቡስ ፕሮጀክት ያላካተታቸው ጠቃሚ ጎኖች በአዲስ አበባ ፕሮጅክት መካተታቸውንም አብራርተዋል፡፡

Leave a Reply