የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን የተሻሻሉ የቅጣት እርከኖችን ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ ከተማን በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ፣ጽዱና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የአረንጓዴ ስፍራዎች ፣ፓርኮች መንገዶች እና የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እየተገነቡ ይገኛሉ፡፡

ይህንን ተከትሎ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነትና የልማቶቹን ዘላቂነት ለማስቀጥል ያግዛሉ የተባሉ አዳዲስ ደንቦች ይፋ ተደርገዋል፡፡

ደንቦችን በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን እና የአዲስ አበባ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ባለስልጣኑ በጽዳትና ተያያዥ ህገ-ወጥ ተግባራት ዙሪያ ቀድሞ ሲጠቀምበት በነበረው ደንብ ቁጥር 150/2015 ላይ የነበረውን የቅጣት እርከኖቹን በማሻሻል ወደ ተግባር መግባቱን ተናግረዋል።

የቅጣት እርከኖቹን ለህብረተሰቡ ዝርዝር መረጃ በመስጠት በመረጃ እጦት ለቅጣት እንዳይዳረግ ግንዛቤ መፍጠር ይገባል ብለዋል።

በዚህም ከ2ሺ ብር እስከ 100ሺህ ብር የቅጣት እርከኖች በግለሰቦችና በተቋማት ላይ መጣሉን ተናግረዋል።

በዚህም መሠረት :-

*ማንኛውም ሰው ያመነጨውን ደረቅ ቆሻሻ በግቢው ውስጥ በአግባቡ አለመያዝ፤በዓይነት አለመለየት፤ ማዝረክረክ፤ ለጤናና የአካባቢ ገጽታ በሚጎዳ መልኩ ማከማቸት፤ ለግለሰብ 2 ሺህ ብር ለድርጅት 50 ሺህ ብር

*ማንኛውም የጽዳት አገልግሎት ሰጭ ድርጅት/ማህበር ደረቅ ቆሻሻ ሲሰበስብ ገጽታ ካበላሸ 25 ሺህ ብር

*በተቀመጠው ስታንዳርድ መሰረት ለደንበኛው ተገቢውን አገልግሎት ካልሰጠ 50 ሺ ብር

*ከጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ እውቅና ውጭ የአገልግሎት ክፍያ ከደንበኛው ከተቀበለ 50 ሺ ብር

*ጊዜያዊ የደረቅ ቆሻሻ ማስቀመጫ ቦታዎችን እስከ 5 ሜትር ዙሪያ ድረስ ጽዱ ካላደረገ 50 ሺ ብር

* ማንኛውም በመንገድ የሚንቀሳቀስ ሰው የሲጋራ ቁርጥራጭ፣ የሶፍት ወረቀት፣ ፌስታል፣ የጫት ገለባ፣ የፍራፍሬ ተረፈ-ምርቶች፣የትራንስፖርት ቲኬት፣የሞባይል ካርዶችን፣ የማስቲካና ከረሜላ ሽፋኖች፣ የመሳሰሉት ጥቃቅን ደረቅ ቆሻሻን ባልተፈቀደ ቦታ ወይም በፓርኮች፣ በአረንጓዴ ቦታ፣ በኮሪደር ከጣለ 2 ሺ ብር

*ከመኖሪያ ቤት ወይም ከድርጅት ግቢ ውጭ ያለውን የአካባቢ ንጹህና አረንጓዴ አድርጎ አለመጠበቅ ከመኖሪያ ቤት አጥር ግቢ ውጭ እስከ 5 ሜትር ርቀት አለማጽዳት፤20 ሺ ብር

*ከድርጅት/ተቋም አጥር ግቢ ውጭ እስከ 10 ሜትር አለማጽዳት፤ 100 ሺ ብር

*ወቅታዊና ልዩ ዝግጅት አከናውኖ በዓሉ ሲጠናቀቅ በዕለቱና ወዲያው ዝግጅቱ የተከናወነበትን አካባቢ ከቆሻሻ ያላጸዳ የፕሮግራሙ አዘጋጅ፤ 50 ሺ ብር

*ዓመታዊ፤ ወርሃዊና ሳምንታዊ የእምነት በዓላት ሲከናወኑ ዝግጅቱ ሲጠናቀቅ የዝግጅቱ ባለቤት በዕለቱና ወዲያው አካባቢውን ካላጸዳ፤20 ሺ ብር የሚቀጡ መሆኑም ተመላክቷል ።

Leave a Reply