የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቦስ አገልግሎት ድርጅት አዲስ የአገልግሎት ህትመት (ትኬት) ጥቅም ላይ ሊያውል እንደሆነ ተገለፀ፡፡

/አዲስ አበባ መጋቢት 18/2016 ዓ.ም/ ድርጅቱ ከአሁን ቀደም ሲጠቀምባቸው የነበሩ ትኬቶችን (ህትመት) ሙሉ በሙሉ በአዲስ ህትመት በመለወጥ ወደ ተግባር ሊገባ እንደሆነ ተገለፀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት አንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት እና ሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ተዋህደው በአዋጅ ቁጥር 74/2014 የተቋቋመ መሆኑን እና ሁለቱ ድርጅቶች ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ትኬቶችን እስከአሁን አገልግሎት ላይ እንደነበሩ የገለፁት የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ግዛው አለሙ ከነገ ሀሙስ (19/2016 ዓ.ም) ጀምሮ አዲስ ህትመቶችን አገልግሎት ላይ ይውላል ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ ለአገልግሎት የሚጠቀምባቸው ትኬቶች ከአሁን ቀደም ከነበሩ የተለዩ እና በዋጋ ወጥነታቸው፣ በቀለማቸው እና በሚስጥራዊነታቸው የተለዩ እንዲሁም ከአሁን ቀደም ከደንበኞች ሲቀርቡ የነበሩትን ችግሮች ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር መሆኑን ዋና ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡

አዲስ ወደ አገልግሎት የሚገቡ ህትመቶች( ትኬቶች) ከሀሙስ ( መጋቢት 19/2016 ዓ.ም) ጀምሮ በአምስቱም ቅርንጫፎች በሁሉም የስምሪት መስመሮች ተግባራዊ እንደሚሆን ገልፀው፤ ደንበኞች በኪሎ ሜትር ትራንስፖርት ቢሮ ባወጣው ታሪፍ መሰረት ተግባራዊ ሲደረጉ በነበሩት የዋጋ ተመን መሰረት የታተሙ የድርጅቱ ትኬቶች (ህትመት) ከአገልግሎት ሂሳብ ተቀባይ (ትኬተሮች) በመግዛት እንዲጠቀሙ አቶ ግዛው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በተጨማሪም ለአገልግሎት የሚውሉ ህትመቶች (ትኬቶች) ባለ አምስት፣ ባለ አስር፣ ባለ አስራ አምስት ሃያ፣ ባለ እና ባለ ሃያ አምስት የዋጋ ተመን (ብር) ያላቸው እና በዋጋቸው ልክ የተለያየ ቀለም እንዳላቸው ህብረተሰቡ በመገንዘብ ለአገልግሎት እንዲጠቀሙ ተመላክቷል፡፡

በቀጣይም ድርጅቱ የህብረተሰቡን እርካታ ከፍ ለማድረግ ዘመናዊ አሰራሮችን እየተገበረ ሲሆን በቅርብ ቀናት ትኬት በቀጥታ አትሞ የሚሸጥ የክፍያ መሰብሰቢያ ዘዴ Handheld ticket terminal (HTT) ቴክኖሎጂ ወደ ተግባር እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

#Addis_Ababa_City_Bus

Leave a Reply