በዛሬ ስብሰባው የከተማዋን አጠቃላይ ልማት እና ሁለንተናዊ እድገት እንዲሁም የነዋሪውን አዳጊ ፍላጎቶች ታሳቢ ያደረጉ ጉዳይ ላይ ተወያይቷል።
ካቢኔው አዲስ አበባ የደረሰችበትን የእድገት ደረጃ የሚመጥን የመንገድ ልማት ኮሪደሮችን ለመገንባት የሚያስችል እቅድ ላይ የተወያየ ሲሆን የከተማዋን አጠቃላይ የመንገድ ሽፋን እና ዘመናዊነት እንዲሁም የትራንስፖርት ፍሰት ወደ ላቀ ደረጃ ሊያሳድግ የሚችል የመንገድ ኮሪደር እና የአካባቢ ልማቶች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
በዚህ መሠረት የሚለሙት የመንገድ ኮሪደሮች የሚከተሉት ይሆናሉ:-
– ከአራት ኪሎ በመስቀል አደባባይ እስከ ቦሌ ድልድይ (7 ኪ.ሜትር)
– ከቦሌ አየር መንገድ እስከ መገናኛ ዲያስፖራ አደባባይ (4.9 ኪ.ሜትር)
– ከመገናኛ ዲያስፖራ አደባባይ በአራት ኪሎ በኩል የአድዋ ድል መታሰቢያ አካባቢ ድረስ (6.4 ኪ.ሜትር)
– ከፒያሳ አድዋ ድል መታሰቢያ ዙርያ፣ በለገ-ሃር ሜክሲኮ፣ በሳርቤት በኩል እስከ ወሎሰፈር (10 ኪ.ሜትር) ናቸው።
እነዚህ የመንገድ ኮሪደር ልማቶች ሁለንተናዊ የመንገድ ዘመናዊነት ያሟሉ ከመሆናቸውም በላይ ዓለም አቀፍ የስማርት ሲቲ ስታንዳርድን በማሟላት የከተማችንን ደረጃ ከፍ የሚያደርጉ ናቸው።
የመንገድ ኮሪደር ፕሮጀክቶቹ አዋሳኝ የወንዝ ተፋሰሶችን ያቀፉ፣ የሳይክልና ሞተር አልባ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ፣ የከተማዋን ማስተር ፕላን እና አርባን ዲዛይን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሁም ለከተማዋ እጅግ ዘመናዊ የትራንስፖርት ፍሰት የሚያጎናፅፉ መሆኑ ታምኖበታል።
በተጨማሪም አስፈላጊ በሆኑ የኮሪደሩ ቦታዎች ላይ ስታንዳርዳቸውን የጠበቁ ተሸጋጋሪ ድልድዮች፣ ማሳለጫዎች እና ሰፋፊ መጋቢ መንገዶችን ያቀፈ ሲሆን የከማ አረንጓዴ ልማትን ያካተተ እንደሚሆንም ታውቋል።
የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔም የቀረበውን የመንገድ ኮሪደር ልማት እቅድ በጥልቀት መርምሮ በሙሉ ድምፅ ያፀደቀ ሲሆን ከነገው እለት ጀምሮ ወደ ስራ እንዲገባና ልዩ ክትትል እንዲደረግለት ወስኗል።