ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ የከተማዋን ገጽታ ለመቀየር እና የከተማዋን ዓለም ዓቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ እየተጋ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2015 ዓ.ም የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን ነድፎ ወደ ተግባር እያስገባ ይገኛል፡፡
ከነዚህም መሃከል በዛሬው እለት የፊርማ ስነስርዓቱ የተከናወነላቸው ሁለት ታላላቅ ፕሮጀክቶች ፡-
በ6 ቢሊዮን በላይ በሆነ ወጪ በተለያዩ ሶስት ቦታዎች (በለሚ ኩራ ክ/ከተማ 2 ፕሮጀክትና ፤ በኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ አንድ ፕሮጀክት) የሚገነባው የግብርና ምርቶች መሸጫ ማእከላት የመጀመርያው ነው፡፡
ሁለተኛው በ1.5 ቢሊዮን በሆነ ወጪ የሚገነባው የዘውዲቱ ሆስፒታል ማስፋፍያ የB+G+8 ፕሮጀክት ግንባታ ነው፡፡
በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምዕራብና በምስራቅ በር ለሚገነቡ ሦስት የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከላት ከተማ አስተዳደሩ 6.1 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን የሜጋ ፕሮጀክቶችን ግንባታ የማስጀመር መረሀ-ግብር ላይ የተናገሩት ከንቲባ አዳነች እስካሁን ባለው በአይነቱ የተለየ ግዙፍ የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከል ባለመኖሩ ማዕከላቱ አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን ተናግረዋል ።
የገበያ ማእከላቱ ግብርና ውጤቶችን በወቅቱ በማቅረብ የአቅርቦት ችግር እንዳይፈጠር በማድረግ የከተማውን ነዋሪ ከኑሮ ውድነት ጫና መታደግ የሚያስችሉ መሆናቸውንና አምራቹም ምርቱን በማቅረብ ተጠቃሚ እንደሚሆንም ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም የገበያ ማዕከላቱ ተጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ ለ30 ሺህ ሰዎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥሩም ተናግረዋል፡፡
የሚገነባውም ኩባንያ በከተማዋ በአጭር ጊዜ ፕሮጀክት በማጠናቀቅ ተሞክሮውን አንስተው አሁንም 24 /7 የመስራት ልምዳችንን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የሆስፒታል ማስፋፊያ ስራው ግዙፍና ከተማዋን የጤና ቱሪዝም ማዕከል የማድረግ ዕቅድ አካል መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባ አዳነች ታሪካዊውና ጥንታዊውን የዘውዲቱ ሆስፒታል ማስፋፊያ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የሆስፒታሉ ሕሙማንን የመቀበልና የማከም አቅም ከፍ እንደሚል ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹን ለመገንባት ውል የወሰዱት ሁለት ኩባንያዎች በበኩላቸው ፕሮጀክቶቹ ለሕዝቡ ባላቸው ፋይዳ ግዙፍ በመሆናቸው የሚያጋጥሙ ችግሮች በመሻገር ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ ለማጠናቀቅ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ የሆስፒታል ማስፋፊያውንና የገበያ ማዕከላቱን ለመገንባት ከ7.6 ቢሊዮን በር በላይ ብር መመደቡ ተገልጿል፡፡