አዲስ አበባ፣ ጥር 27 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የመሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮና ተጠሪ ተቋማቱን የስድስት ወራት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን ገመገመ::
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ የግማሽ በጀት ዓመቱን የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን፤ በሪፖርቱም የአዲስ አበባ ምክር ቤት የመሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በክትትልና ድጋፍ ወቅት በተሰጡ ግብረመልሶችን መሰረት በማድረግ የተሰሩ ስራዎችንና የመጡ ለውጦችን በሪፖርቱ ቀርቧል።
በሪፖርቱም በዋናነት የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር በለስልጣንን የማዘመን፣ የህዝብ ትንስፖርት ተርሚናልን የማስፋት፣ የግል ባለሀብቱን ተሳትፎ የማሳደግና የትራፊክ አስተዳደር ስርዓቱን በማዘመን ከተማዋን የሚመጥን የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተጠቅሷል።
የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አባላት በእቅድ ተይዘው የተከናወኑ ተግባራትንና እቅድ አፈጻጸማቸውን በጋራ የገመገመ ሲሆን፤ በዘርፉ እየተመዘገቡ ያሉ ለውጦች አበረታች እንደሆኑ በመግለጽ በዘርፉ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል የቆይታ ጊዜን ማሻሻል፣ በዘርፉ የግል ባለሀብቱን ማሳተፍ እንደሚገባ ገልፀዋል።
በተጨማሪም ከህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ የስነ ምግባር ችግሮች በተለይ ከታሪፍ በላይ ማስከፈልና የመስመር ማቆራጥ፣ አውተኦቡሶች ለረጅም ጊዜያት ተሳፋሪ እያለ መቆም፣ የአገልጋይነት መንፈስ አነስተኛ መሆን፣ እንዲሁም ከታክሲ ተራ አስከባሪዎች እና የፖርኪንግ አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ በቀጣይ ቢሮው ትኩረት ሰጥቷ መስራት እንደሚገባው ተጠቁሟል::
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የመሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ልዕልቲ ግደይ በዘርፉ የሚሰጠውን አገልግሎት የተሻለ ለማድረግ በስድስት ወሩ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆኑንና የመጡ ለውጦችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ በመግለፅ፤ ሌብነትና ብልሹ አስራርን ቀዳሚ ስራ በማድረግና በመታገል ውጤታማ የሆነ ተቋም መገንባት እንደሚያስፈልግ በአንክሮ ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ የመሰረተ ልማት ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዘርፉን የተሻለ ለማድረግ እየተደገ ያለው ክትትልና ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባና በውይይቱ የተነሱ ገንቢ አስተያየቶችን በመውስድ ቢሮው ከተጠሪ ተቋማቱ ጋር በጋራ ይሰራል ብለዋል።
በውይይቱም የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የመሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት፣ የክፍለ ከተማ ዘርፉ ኮሚቴ አመራሮች፣ የህዝብ ክንፋ አመራሮችና የትራንስፖርት ቢሮና ተጠሪ ተቋማት አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።