አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 09፤ 2015ዓ/ም
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ በከተማዋ የትራንስፖርት አሰጣጡ አስተማማኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ተደራሽ፣ ወጪ ቆጣቢና አካባቢያዊ ተስማሚነቱ የተረጋገጠ ትራንስፖርት እውን ለማድረግ እንዲቻል የከተማ ፈጣን አውቶብስ ትራንዚት (BRT) ልማት ፕሮጀክቶችን ቀርጾ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ቢሮው ዘርፉን በተሻለ እውቀት ለመምራት Institute for Transport and Development Policy (ITDP) ከተባለ አለም አቀፍ ድርጅት ጋር በጋራ በመተባበር የBRT ዲዛይን እና ኦፕሬሽን ላይ በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት በዘርፉ ለሚገኙ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥቷል፡፡
ስልጠናው በዋናነት ትኩረት ያደረገው የትራንስፖርት ዘርፉ በከፍተኛ የቴክኒክና ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች እና አመራሮች ለመምራት እንዲሁም ለማስተግበርና ለመደገፍ እንዲቻል ትልቅ አቅም ለመፍጠር እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፤ ስልጠናውን ያዘጋጀው ተቋም በBRT ዙሪያ የሚሰጡ ስልጠናዎች በቀጣይም እንደሚኖራቸው እና ዘርፉ የሚመለከታቸው ተቋማት አመራሮችን እንዲሁም ባለሙያዎችን አቅም ለመገንባት እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡
የትራንስፖርት ቢሮ የመሰረተ ልማት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አካሉ አሰፋ ስልጠና በጣም አስፈላጊና ችግር ፈቺ መሆኑን በመግለፅ የተጀመሩ የBRT ፕሮጀክቶችን በተሰጠው ስልጠና አጋዥነት በጥራትና በጊዜው በማጠናቀቅ የአዲስ አበባ ከተማን የትራንስፖርት ችግር ለመፍታት ከ ITDP እና አጋር ድርጅቶች ጋር ቢሮው በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
በስልጠናውም ከትራንስፖርት ቢሮ የተውጣጡ አመራሮችና ባለሙያዎች፣ የሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት፣ የአንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ፣ የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን፤ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ጽ/ቤት፣ የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን እና Agencia Franciane De Development /AFD/ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በመጨረሻም ስልጠናው ላይ ለተሳተፉ አመራሮችና ባለሙያዎች የምስክር ወረቀት በቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ወርቁ ደስታ እና በአይቲዲፒ አፍሪካ ዳይሬክተር በሆኑት Mr. Christopher Kost እጅ ተረክበዋል፡፡
ዘገባው፡-በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነው፡፡
ለበለጠመረጃ፡- ነፃ የስልክ መስመር 9417 ይጠቀሙ!
የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረገጽ፦ https://www.aatb.gov.et