አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፤ 2015 የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኮልፌ፣ ጉለሌ፣ አራዳ፣የካ፣ ንፋስ ስልክ፣ ለሚኩራና አቃቂ ቃሊቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ከአዋሳኝ ልዩ የአሮሚያ ዞን ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጠናከር እንዲሁም በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችና የመፍትሄ ሀሳቦች ዙሪያ መከረ፡፡
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የከተማዋን የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሀዊና፣ደንብና መመሪያና የተከተለ አሰራር ተከትሎ ለመስራት እንዲያስችል ትራንስፖርት ቢሮው ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ትራንስፖርት ቢሮ ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሰራር እየተጠናከረ የመጣ መሆኑንና በወቅታዊና ሀገራዊ ስራዎች ተቀናጅቶ ተልዕኮዎችን በጋራ ተናቦ የመፈፀምና የማስፈፀም ሂደቱ መልካምና የዘርፉ አሰራር የተሻለና ውጤታማ እንዲሆን ያረገው ቢሆንም፤ አሁንም ወጥ በሆነ አሰራር ትራንስፖርቱን ከመምራት አንጻር የሚታዩ ክፍተቶች መኖራቸው በተደረገው የውይይት መድረክ ተገልጿል፡፡
በውይይቱም በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ልዩ ዞን ትራንስፖርት ዙሪያ እየተሰጡ የሚገኙ ችግሮች የተነሱ ሲሆን ከቁጥጥር፣ ከስምሪት ስርዓትና ከተማሪ ሰርቪስ ፍቃድ አሰጣጥ ጋር ያሉ ችግሮችና የታሪፍ ወጥና ተናባቢ አለመሆን እንዲሁም ሌሎችም መፈታት ያለባቸው ችግሮች በተወያዮቹ ተጠቁሟል፡፡
በአገልግሎት አሰጣጡ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ሁለቱም ቢሮው የመረጃ ቅብብሎሹን በተጠናከረና የግንኙነት ጊዜ አግባብን በማስቀመጥ በመመሪያ ደረጃ የሚቀመጡ አሰራሮችን በጋራ ተፈጻሚ በማድረግ በጋራ የተቀናጀ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡
በእለቱ የነበሩ የትራንስፖርት ቢሮ የቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊዎች የህዝብ ትራንስፖርት አቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም፣ የትራፊክ ፍሰት ከመጠን በላይ መሆን፣ የደንብ ተላላፊዎች መበራከት፣ መስመር አለመሸፈን፣ መስመር ማቆራረጥ፣ ያለፈቃድ መስራት፣ ህገ ወጥ ተርሚናሎች እና ተራ አስከባሪዎች መበራከት፣ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፣ በጎዳናዎች ላይ ህገ ወጥ ንግድ መስፋፋት፣ የመንገድ መቆፋፈር ወይም ከፍተኛ የሆነ የመንገድ ብልሽት፣ ፣ የተርሚናል ጥበት፣ የህብረተሰብ መስመር ይከፈትልንና የመሳሰሉት ችግሮች በሰፊው እየተስተዋሉ በመሆኑ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ውይይቱ ወሳኝነት እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
በውይይቱም የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊዎች፣ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የሴክተሩ አመራሮች፣ አንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት፣ ሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት፣ ትራፊክ ፖሊስ መምሪያና የተቋማት ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ዘገባው፡-በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነው፡፡
ለበለጠመረጃ፡- ነፃ የስልክ መስመር 9417 ይጠቀሙ!