አዲስ አበባ፣ ህዳር/2015፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ የ2015 በጀት አመት የአራት ወር የዕቅድ አፈፃፀሙን ከባለድርሻና ተገልጋይ አካላት ጋር ገመገመ፡፡
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የእቅድና በጀት ዳይሬክቶሬት አቶ ይታያል ደጀኔ ቢሮው በተግባር ምዕራፍ የተተገበሩ ዋና ዋና ስራዎችን በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን፤ የብዙሀን ትራንስፖርት አቅርቦትና ሽፋንን በማሳደግ በአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ዘርፍ አገልግሎቱን ለማዘመን እንዲሁም የትራንስፖርት መሰረተ ልማትን በማልማትና በማስተዳደር የተሰሩ ስራዎችና የትራፊክ ደህንነት ማሻሻያ ላይ ትኩረት ተደርጎ የተሰሩ ስራዎችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊ የሆኑት የታክሲ ባለንብረት ማህበራት አመራሮች በቀረበው ሪፖርት ዙሪያ መነሻነት ጥያቄዎች ያነሱ ሲሆን በዋናነትም ወደ ብዙሀን ትራንስፖርት ሽግግር ለማድረግ የቢሮውን ድጋፍ እንደሚሹ፣ የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የአገልግሎት ክፍያና የኮቪድ ፕሮቶኮል የቅጣት ክፍያ አፈፃፀም ጋር ተያይዞ ቅጣቱ ህዝብ ትራንስፖርትን ያገናዘበ እንዲሆንና በተመሳሳይ ከታለመለት የነዳጅ ድጎማና ከቴሌ ብር ጋር ተየይዞ ያሉ ክፍተቶች፣ የህንጻ ስር ፖርኪንግ፣ የወጡ ደንቦችን የማስተግበርና የክትትል ስራም በመድሪኩ ተነስተዋል::
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ ቢሮው የብዙሀን ትራንስፖርት ተደራሽነትን ማስፋት፣ አገልግሎት አሰጣጡ ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን በማድረግና መጠነ ሰፊ የሆነውን የህዝብ ትራንስፖርት ጥያቄዎችን ለመመለስ፣ ትራፊክ ፍሰቱን እና አደጋዎችን ከመቀነስ አንጻር በዘርፉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪ በዘርፉ የተለዩ የመልካም አስተዳደርና የብልሹ አሰራር ከዘርፉ ተጠሪ ተቋማትና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የተናበቡ እቅዶችን በማቀድና በመተግበር እንዲሁም ቋሚ የግንኙነት ጊዜን በማስቀመጥ በትኩረት እንደሚሰራ በመግለፅ ዘርፉን ወደ ተሻለ አፈጻጸም ለማምጣት ሁሉም የዘርፉ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት በጋራ መስራት እንደሚገባቸው በአንክሮ ገልፀዋል፡፡
በውይይቱም የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የስራ ኃላፊዎች፣ የአስራ አንዱም የትራንስፖርት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊዎች፣ የቢሮው ተጠሪ ተቋማት፣ የታክሲና የሀይገር ማህበራት አመራሮች፣ የአዲስ አበባ ትራፊክ መምሪያ ፖሊስ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ከንቲባ ፅህፈት ቤት፣ የትራንስፖርት ተገልጋይና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡