አዲስ አበባ፤ ግንቦት 01፤ 2015 ዓ.ም፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር የትራንስፖርት ቢሮ ባለፈው ክረምት ወቅት በመዲናዋ ገላን የጋራ መኖሪያ መንደር አካባቢ የተከላቸውን ችግኞች የእንክብካቤ ስራ ዛሬ አከናውኗል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ የኦፕሬሽን ዘርፍ ም/ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ዳዊት ዘለቀ እንደተናገሩት እንደሀገር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ያስጀመሩትን የአረንጓዴ አሻራ የማሳረፍ መረሃ-ግብር መሰረት በማድረግ ባለፈው ዓመት ችግኝ መተከሉን በማስታወስ ለምንተክላቸው ችግኞች ተከታታይነት ያለው እንክብካቤ ሊደረግላቸው ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
እንደትራንስፖርት ቢሮ በዚህ ጉዳይ ላይ ድርብ ኃላፊነት አለብን ያሉት ኢንጂነር ዳዊት የአረንጓዴ አሻራ ከማሳረፍ ባሻገር ከተሽከርካሪ የሚለቀቀውን የበካይ ጋዞች ልቀት ለመቀነስ ቢሮው በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
እንደከተማችን ተጨባጭ ሁኔታ 66 በመቶ የአየር ብክለት መንስኤው ከተሽከርካሪዎች የሚለቀቅ በካይ ጋዝ መሆኑን የተናገሩት ም/ቢሮ ኃላፊው ይህንን የበካይ ጋዞች ልቀት መጠን ለመቀነስ ችግኞችን መትከልና መንከባከብ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡
አያይዘውም በዓመት አንድና ሁለት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በየወሩ ፕሮግራም ተይዞለት የችግኝ እንክብካቤ ስራው ተከታታይነት ባለው መልኩ መከናወን እንዳለበትም ኢንጂነር ዳዊት አፅንኦት ሰጥተው አስታውቀዋል፡፡
በዚህ ረገድ ችግኞችን በመንከባከብ የፅድቀት መጠናቸውን በማሳደግ ከተሸከርካሪዎች የሚለቀቁ የበካይ ጋዞችን ልቀት መጠን ለመቋቋም በሚደረገው ስራ ላይ የቢሮው ሚና የጎላ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡
ቢሮው ከ20 ሺህ በላይ ችግኞችን ባለፈው የክረምት ወቅት ሠራተኞችን በማስተባበር ተከላ ማካሄዱ የሚታወስ ነው፡፡
ዘገባው፦ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ነው
ለበለጠ መረጃ፦ 0116663374 ወይም በነፃ የስልክ ጥሪ መስመር 9417 ይጠቀሙ!