የአዲስ አበባ ፖሊስ የህዝብ የጋራ መገልገያ በሆኑ የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች አስቀድሞ ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ኬብሎች ላይ የስርቆት ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦችን ይዞ በህግ እንዲጠየቁ እያደረገ መሆኑም ይታወሳል፡፡
ቴዎድሮስ ግዛው የተባለው ግለሰብ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ቦታው ልደታ የባቡር ፌርማታ አካባቢ ከሌሊቱ 7 ሰዓት ላይ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት የኃይል ማስተላለፊያ እና የመገናኛ ኬብሎችን እየቆረጠ ሲሰርቅ በፖሊስ አባላት እጅ ከፍንጅ መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ግለሰቡ በፈፀመው ወንጀል በድርጅቱ ላይ የ8 ሚሊዮን 4 መቶ ሺ ብር ጉዳት ማድረሱ የተረጋገጠ ሲሆን በልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የባልቻ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ አስፈላጊውን ምርመራ በማጣራት በግለሰቡ ላይ ክስ እንዲመሰረት አድርጓል፡፡
የተከሳሹን ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ልዩ ልዩ ወንጀል ችሎት ግለሰቡ በ6 ዓመት ከ6 ወር እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡
ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ በተገነቡ ልዩ ልዩ የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ የሚፈፀም የስርቆት ወንጀል በማህበረሰቡ የእለት ከእለት እንቅስቃሴ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ወንጀሎችን አስቀድሞ በመከላከል ረገድ ህብረተሰቡ እና ባለድርሻ አካላት ከፀጥታ ሃይሉ ጎን በመሆን ወንጀሉን ሊከላከሉት እንደሚገባ መልዕክት ያስተላለፈው የአዲስ አበባ ፖሊስ፤ በተለይ የተሰረቁ የመሰረተ ልማት አውታሮችን የሚገዙ ግለሰቦች ወንጀሉ እንዲስፋፋት እያደረጉ በመሆኑ ከህገ-ወጥ ተግባራቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
@አዲስ አበባ ፖሊስ