(ሚያዚያ 03/2016 ዓ.ም)፡- በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ምክር ቤት የ2016 በጀት ዓመት የ9 ወራት የእቅድ አፈጻጸምና በቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች ዙሪያ የምክር ቤቱ አባላት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን፣ የሚዲያ አካላት፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተወያይተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖት ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ የውይይቱን መርሃ ግብር በንግግር ሲከፍቱ እንዳሉት በከተማዋ የተሽከርካሪ እና የህዝብ ቁጥር በመጨመሩ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴው ማደጉ ለትራፊክ ግጭት ቁጥር መጨመር ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ገልፀዋል።
በ2016 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት 286 ሰዎች በመንገድ ትራፊክ ግጭት ህይወታቸውን እንዳጡና ምንም እንኳን ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 9 ሰው መቀነሱን ቢያሳይም በተለይ የትራፊክ አደጋው አምራች የሆነውን ወጣቱን ሀይል እያሳጣ መሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል ብለዋል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በከባድና ቀላል አካል ጉዳቶችም መጠነኛ ቁጥሮች መቀነስ እንደሚታይና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በከተማ አስተዳደሩ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ በተለይም የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ በመንደፍና በከንቲባ ደረጃ የሚመራ ምክር ቤት በማቋቋም የትራፊክ አደጋን ለመከላከል በርካታ ተግባራት እንደተከናወኑ አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር እና የመንገድ ደህንነት ምክር ቤቱ ጸሃፊ አቶ ክበበው ሚደቅሳ የመንገድ ደህንነት ምክር ቤት አባል ተቋማት የ2016 በጀት ዓመት የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ በሪፖርት ካቀረቡት ውስጥ በመንገድ ትራፊክ ደህንነት አስተዳደር ስርዓት መገንባት፣ የትራፊክ አደጋ በሚበዛባቸው ዋና ዋና መንገዶች ላይ ማሻሻያ መስራት፣ የፓርኪንግ መሰረተ ልማቶች፣ የግንዛቤና አቅም ግንባታ ስራዎች፣ የደንብ ማስከበር ተግባራት፣ የድህረ አደጋ ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ እና የትራፊክ አደጋ መረጃ አያያዝና ሪፖርት አዘገጃጀት ተግባራት አፈፃፀም ይገኙበታል።
ከሪፖርት በኋላም የመንገድ ትራፊክ አደጋ በመቀነስ ስራ ውስጥ የቅንጅታዊ አሰራር አጠናክሮ እና ተደጋግፎ ክፍተቶችን ሞልቶ ቢሰራ፣ አሽከርካሪዎችን ብቻ ሳይሆን እግረኞችም ሲያጠፉ መቅጣት ላይ እርምጃዎን ማጠናከር የሚቻልበት ሁኔታ ቢመቻች፣ የሚሉ አስተያየቶች ቀርበዋል፡፡
የአለም አቀፍ ምልክትና ማመላከቻዎችን እና የትራክ መብራት ሰዓት አቆጣጠርን መለስ ተብሎ ቢታይ፣ የመንገድ ትራፊክ ደህንነትና ቁጥጥር ስራችን ከተማን በሚመጥን የቴክኖሎጂ ግበዓቶች በማሟላት ቢሰራ፣ እግረኞችን ከመቅጣታችን በፊት አስፈላጊውን መሰረተ ልማት ቢሟላላቸው፣ የፍጥት መገደቢያ ጉብታዎች በስታንዳርዳቸው ቢሰሩ የሚሉ ሀሳቦችም ተነስተዋል።
በፕሮግራሙ ማጠቃለያ በስራ ሃላፊዎች ከቤቱ የተነሱ ገንቢ ሃሳብ አስተያየቶችን በግብዓትነት ተወሰደው በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ውስጥ ተካተው እንደሚሰሩና በ9 ወራት ውስጥ ስራቸውን በጥንካሬ ለተወጡ የምክር ቤት አባላትና ተቋማት ምስጋና በማቅረብ በቀጣይ ሁሉም አካላት በመረባረብ የዜጎችን ህይወት፣ አካልና የንብረት ጉዳት በጋራ እንከላከል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡