መስከረም 30/2015ዓ.ም፤ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አቃቂ ቃሊቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ከአንበሳ ከተማ አውቶብስ ድርጅት፣ ከትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ፣ ከአዲስ አበባ ትራፊክ ፖሊስና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ቀደም ሲል በመንገድ ግንባታ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የአንበሳ ከተማ አውቶብስ የመስመር ቁጥር 4 ከቃሊቲ መርካቶ ዛሬ በአዲስ መልኩ ዳግም አገልግሎት እንዲሰጥ አደረገ፡፡
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አቃቂ ቃሊቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ኢንስፔክተር ቶማስ ሂርጳ ህብረተሰቡ በመስመር ቁጥር 4 ሲሰጥ የነበረው አገልግሎት በመቋረጡ ለእንግልት መዳረጉን ለቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ ጥያቄ ማቅረቡን አስታውሰው፤ ዛሬ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራሮችን በመፍጠር ሰባት አውቶብሶችን በቦታው በመመደብ አገልግሎቱን እንዲሰጡ በማድረግ ምላሽ መስጠት መቻሉን ገልፀዋል፡፡
ኮማንደር ጥላሁን ፀጋዬ የኮሜርሻል ኖሚኒስ ጀነራል ዳይሬክተርና የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል በአከባቢው የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚው ህብረተሰብ ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ ትራንስፖርት ቢሮ ባለው የትራንስፖርት አቅርቦት ለህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ችግር የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት ለጥያቄዎች ምላሽ መስጠቱንና ህብረተሰቡ ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ አቅርቦት የለም ሳይሆን አቅርቦቱን ጨምሩልን ማለት መጀመሩ ቢሮው ውጤታማ ስራ መስራቱን ማሳያ መሆኑን ገልፀው፤ ምክር ቤቱ በትራንስፖርቱ ዘርፍ መደገፍ ያለበትን ሁሉ እንደሚደግፍ ቃል ገብተዋል፡፡
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና አፈ ጉባኤ ሙሉጌታ አሰፋ ከመሰረተ ልማት ጋር በተገናኘ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አውቶብሶችና ታክሲዎች መብራት ባለመኖሩ ምሽት ለእይታ እየተቸገሩ በመሆኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በዘለቄታዊ መንገድ መፍትሄ እስኪሰጥ በጊዚያዊነት ከመንገድ ዳር የተለያዩ አገልግሎት በመስጠት ላይ ከሚገኙ አካላት መብራት መጋራት እንደሚቻልና ስራውንም በባለቤትንት እንደሚሰሩ አሳውቀዋል፡፡
የአንበሳ ከተማ አውቶብስ መስመር ቁጥር 4 ተገልጋዮችም አገልግሎቱ በመቋረጡ ተቸግረው መቆየታቸውንና አገልግሎቱ በተመጣጣኝ ታሪፍ በመጀመሩ መደሰታቸውን በታላቅ ደስታ ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም በቦታው ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ትራንስፖርት ፍላጎት በመኖሩ ከፍላጎት አንጻር በቂ ቁጥር ያለው ተጨማሪ አውቶብስ ቁጥር በቀጣይ እንዲጨመር ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ለባስ ብቻ የተፈቀደ መንገድ የሚል ምልክትና ማመላከቻ በቦታው ላይ እንዲተከልና የአቃቂ ቃሊቲ የመንገድ ግንባታ ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ አውቶብሶቹ በቀኝ በኩል በተጠናቀቀው መንገድ አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ሰላማዊ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖር በእለቱ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡