አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፤ 2015 በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ በትራንስፖርት ዘርፉ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍና የተማሪዎች ትምህርት መጀመርን በማስመልከት የህዝብ ትራንስፖርት አሰጣጡን ቀልጣፋ፣ ፈጣን ፣ ውጤታማ እና ተደራሽ ለማድረግ ቢሮው በመስከረም ወር መጀመሪያ ያቋቋመው የሱፐርቪዥን ቡድን የአንድ ወር የስራ አፈጻጸሙን ገመገመ፡፡
የሱፐር ቪዥን ቡድን ምክትል ሰብሳቢ አቶ አምባላይ ዘርዓይ በዘርፉ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ለመደገፍ የተሰሩ ስራዎች አበረታች መሆናቸውንና ባሉት ተሽከርካሪዎች የተሻለ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት በአስራ አንዱም (11) ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ያሉ የስምሪትና ቁጥጥር ባለሙያዎችና የስራ ኃላፊዎች ጠዋት ከ12፡45 ጀምረው በተመደቡበት የስራ መስክ በመገኘት በአገልጋይነት መንፈስ አገልግሎት መስጠት መቻላቸው አበረታችና መቀጠል ያለበት ተግባር ነው ብለዋል።
በተጨማሪም የመልካም አስተዳደር ችግር አለባቸው ተብለው የተለዩ መስመሮችንና ተርሚናሎች ላይ ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ፣ የአቴንዳንስ አያያዝን ወጥና ፍትሀዊ ማድረግ፣ በአጥፊ አሽከርካሪዎች ላይ የአገልጋይነት መንፈስ ለመፍጠር መሰራት ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር መሆኑም በግምገማው ተገልፆል፡፡
ቡድኑ በየቀኑ ለቅርንጫፍ ዳይሬክተሮች፣ ቡድን መሪዎች፣ አስተባባሪዎች እንዲሁም ለቁጥጥሮች የሚታዩ ክፍተቶች በመናገር እንዲፈቱ በማድረግና ያልተፈቱትንና ከአቅም በላይ የሆኑትን ደግሞ ለሚመለከተው የበላይ አካል ሪፖርት እየተደረገ የትራንስፖርት አገልግሎቱን በተለይ የተሳፋሪ የቆይታ ጊዜ ለመቀነስና ለማሳጠር፣ በትራንስፖርት አገልግሎቱ ላይ ደንብ የሚተላለፉ አካላት ህግና ስርዓቱን አክብረው እንዲሰሩ ማድረጉ አበረታች መሆኑን የቢሮ የትራንስፖርት አገልግሎት ክትትልና ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ገልፀዋል፡፡
ህብረተሰቡም አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያችን ማገዝና ከተቀመጠው ህጋዊ ታሪፍ በላይ ሲጠይቅ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ መስጠትና ታሪፍ ሳይለጥፍ የአገልግሎት ክፍያ ለሚጠይቅ አገልግሎት ሰጪ ክፍያ መፈፀም የሌለበት መሆኑን የሱፐር ቪዥን አባላት ገልፀው፤ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰሩብቸው ይገባሉ ያሏቸውን አስራ ሁለት ነጥቦችን በመለየት የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን የተሻለና የተቀላጠፈ ለማድረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ በግምገማው ተዳሷል፡፡