አዲስ አበባ፤ ህዳር 27፤ 2015 ዓ.ም፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ በዓለም ለ35ኛ በሀገራችን ለ34ኛ ጊዜ የሚከበረውን የኤች አይ ቪ ቀን “ፍትሀዊና ተደራሽ የኤች አይቪ ኤድስ አገልግሎት” በሚል መሪ ቃል በድምቀት አከበረ፡፡
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የጥናትና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ ወርቁ ደስታ የኤች አይ ቪ ስርጭትን ለመግታት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል አስፈላጊውን ጥንቃቄና ስለ ቫይረሱ ስርጭት በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው መስራት ይገባል ብለዋል።
በተለይ ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የስራ መስኮችንና የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት በቫይረሱ የሚሞተውን አምራች ሀይል ለመታደግ የበኩላችንን ሚና እንወጣ ሲሉም አሳስበዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የስርዓተ ፆታ ባለሙያ ወ/ሮ አመለወርቅ ብርሃኑ የእለቱን የስልጠና ሰነድ ለሰራተኛው ያቀረቡ ሲሆን፤ በሀገር ደረጃ በተለይ አዲስ አበባ የኤች አይቪ ኤድስ ህሙማንና ተጠቂዎች ቁጥር ከሌሎች ክልሎች ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የማህበረሰብ የለውጥ አቅምን በማሳደግና በማጎልበት እንዲሁም ሁሉም ህብረተሰብ የኤች አይቪ ኤድስ ምርመራ በማድረግ እራሱንና ወገኑን ከበሽታ መታደግ እንዳለበት በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡
የስልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ስርጭትና ችግሩ እንደ ህዝብ ጭምር የሚጎዳ በመሆኑ በመንግስት ትኩረት ሊሰጠውና በአመት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን፤ ተከታታይነት ያለው ትምህርትና ውይይት የሚያስፈለገው ትውልዱን የማዳን ተግባር መሆኑን በአስተያየታቸው አንስተዋል፡፡