በከተማዋ በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ ውብ፣ ምቹና ዘመናዊ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ሀብት የሆነው የህዝብ ትራንስፖርት መጠለያዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከቢሮው ጋር በቅንጅት በመስራት አስፈሊውን ጥበቃና እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባ የአቃቂ ቃሊቲ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ገለፀ፡፡
የአቃቂ ቃሊቲ ትራንስፖርት ቅርንጫ ፅህፈት ቤት ይህንን የገለፀው ዛሬ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው የ2015 በጀት አመት የግማሽ በጀት አፈጻጸሙን በገመገመበት ወቅት ነው፡፡
በሪፖርቱም በዋናነትም ከትራንስፖርት አቅርቦት፣ ምልልስና ቁጥጥር አኳያ በግማሽ ዓመቱ የነበረውን የስምሪት ቁጥጥር፣ የትራንስፖርት መጠበቂያ መጠለያዎችን የክትትልና የቁጥጥር ስራ፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር የነበረ ቅንጅታዊ ሥራ ፣ ብልሹ አሰራርና ሌብነትን ከመታገል አንጻር ለአምስት ሰራተኞችን ተጠያቂ ማድርጉን፣ በ4,858 አጥፊ አሽከርካሪዎች መስመር በማቆራረጥ፣ ከታሪፍ በላይ በማስከፈል፣ታፔላ ባለመስቀልና ተሳፋሪን በማጉላላት የእርምት እርምጃ በመውሰድ በስድስት ወሩ በቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ 4,490,460.00 (አራት ሚሊዮን አራት መቶ ዘጠና ሺ አራት መቶ ስልሳ ብር) መሰብሰብ መቻሉ ተገልፆል፡፡
የአቃቂ ቃሊቲ ትራንስፖርት ቅርንጫ ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ ኢንስፔክተር ቶማስ ሄርጶ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ በስድስት ወሩ በርካታ ውጤታማ ስራዎች መስራቱ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር በመጠናከሩ መሆኑን በመግለፅ በክፍለ ከተማው ከሚገኙ 78 (ሰባ ስምንት) የህዝብ ትራንስፖርት መጠለያች ውስጥ ስድስት ወራት ውስጥ 14 መጠለያዎች ከፍተኛ የሆነ ስርቆትና ጉዳት መድረሱንና የህዝብ ትራንስፖርት መጠለያዎች ለታለመላቸው አላማ እንዲውሉ ችግሩን በጋራ ለመቅረፍ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
የመሰረተ ልማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ የውብነሽ ተክሌ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር ስራዎችን ተናቦ ለመስራት እያደረገ ያለውን ስራ አድንቀው በክፍለከተማው ከባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን እንዲፈታ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ በመጀመሪያ መንፈቀ ዓመት በአፈጻጸማቸው የተሻለ የእቅድ አፈጻፀም ለነበራቸው ፈጻሚዎች የእውቅናና የማበረታቻ ሽልማት የተሰጠ ሲሆን የቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ ባለድርሻ አካል የሆኑ የክፍለ ከተማው የፖሊስ አባላት፣ የታክሲና የሀይገር ባለንብረቶች ማህበ፣ የተራ አስከባሪና ከተቋሙ ጋር በበጎ ፍቃደኝነት እየሰሩ ላሉ ግለሰቦች ጭምር የምስጋናና የእውቅና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በውይይቱም የአቃቂ ቃሊቲ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሠራተኞችና አመራሮች፣ የአቃቂ ቃሊቲ ፖሊስ መምሪያ ሃላፊዎችና አባላት፣ የክፍለ ከተማው ሰላምና ፀጥታ ቢሮ፣ የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ተወካይ ፣ የክፍለ ከተማው የትራፊክ ፖሊስ መምሪያ ሃላፊዎችና አባላቶች፣ የክፍለ ከተማው ተራ ማስከበር ኢንተርጵራይዝ ማህበራት፣ የክፍለ ከተማው አፈጉባዔ፣ የመሠረተ ልማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ የክፍለ ከተማው ሠላምና ፀጥታ ፅህፈት ቤት ሃላፊ፣ የታክሲ ማህበራት አመራሮች፣ የትራንስፖርት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጆች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡