አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 30/2015 ዓ.ም የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ዛሬ የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀሙን ከአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን፣ ከትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ፣ ከቀላል ባቡርና ከከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ጋር በትላንትናው እለት በጋራ ገምግሟል፡፡
የቢሮው እቅድና በጀት ዳይሬክተር አቶ ይታያል ደጀኔ የቢሮውንና የተጠሪ ተቋማትን የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን፤ በቀረበው ሪፖርት ላይም ውይይት ተደርጓል።
በሪፖርቱም በእቅድ ተይዘው የተከናወኑ ተግባራትንና እቅድ አፈጻጸማቸውን የተገመገመ ሲሆን፤ በዘርፉ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የተሰሩ ስራዎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል የተገልጋዩን እርካታ ለማሳደግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች፣ ብልሹ አሰራርን በመታገል የተጠያቂነት ስርዓት በመዘርጋት ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ እንደነበር ተገልጿል፡፡
በተመሳሳይ የብዙሀን ትራንስፖርት አቅርቦትን የማሳደግ ስራ፣ የፈጣን አውቶቡስ ትራንስፖርት መሰረተ ልማት የማስፋፋት ስራ መከናወን፣ በዋናነትም በአማካይ በየቀኑ 11,435 ተሽከርካሪዎች ማሰማራት መቻሉን፣ በዘጠኝ ወሩ ወደ አሽከርካሪና ተሽከርካሪ ጉዳይ አገልግሎት ፈልገው ለመጡ 937,091 አገልግሎት ፈላጊዎች አገልግሎት መስጠት መቻሉ፣ ባለው የትራንስፖርት አቅርቦት በቀን 3.13 ሚሊየን ጉዞ መፈጠር መቻሉን፣ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ለማሻሻልና በመንገድ አጠቃቀም ዙሪያ ግንዛቤ መፈጠሩ፣ የአቅም ግንባታ ስራዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ በተሻለ መልኩ መፈፀሙ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ በዘርፉ የሚሰጠውን አገልግሎት የተሻለ ለማድረግ በዘጠኝ ወሩ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆኑን በመግለፅ፤ ዘርፉን በቴክኖሎጂ በማዘመን የከተማዋን እድገት የሚመጥን የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባና የተገልጋይ እርካታን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ ዘርፉን መምራት እንደሚገባ በአንክሮ ገልፀዋል።
የቢሮውና የተጠሪ ተቋማት አመራሮችም በተቋሙ በዘጠኝ ወራት የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ገልፀው፤ በቀጣይ ቢሮው ሊፈታቸውና ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ ተግባራት ዙሪያ እንዲሁም የዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል መሰራት ባሉባቸው ስትራቴጂክ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ መክረዋል፡፡
በመጨረሻም ቢሮው የተቋማትን አደረጃጀት እንደገና በመከለስና ሪፎርም በማድረግ አዳዲስ አመራሮችን መመደቡን ገልፆ፤ ምቹ የስራ አከባቢን የመፍጠር፣ የሰው ተኮር የልማት ስራዎችን የመተግበር፣ በበጀት አመቱ በእቅድ ተይዘው ያልተከናወኑ ተግባራትን በፍጥነት በመለየት በቀሪ ወራት መተግበር እንደሚገባና ቅንጅታዊ አሰራርን በበለጠ አጠናክሮ መሄድ እንደሚገባ ጠቁሟል።