የቦሌ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ከታክሲ ተራ አስከባሪ ዙሪያ የሚስተዋሉ ህገወጥ ተግባራትን ለመከላከል በክፍለ ከተማው ካሉ 250 የታክሲ ተራ ማስከበር ማህበራት ጋር ትላንት በቦሌ ክፍለ ከተማ የመሰብሰብያ አዳራሽ በጋራ መክሯል።
የቦሌ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ታረቀኝ ለውይይት መነሻ የሚሆን ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን፤ በሰነዱ በዋናነት ህዝብን ማገልገል ቅድሚያ የሚሰጠው ትልቅ ኃላፊነት ነው ብለዋል።
በተመሳሳይም የደንብ ልብስና ባጁ አለማድረግ፣ እላፊ ተጠቃሚነት ፣ የስነምግባር ችግርና በአንዳንድ ተርሚናል ለህገወጥ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ተባባሪ መሆን እየተበራከተ መምጣቱና እየተሰሩ ያሉ መልካም ስራዎችም በሰነዱ ተጠቅሷል።
የፅህፈት ቤት ኃላፊውም የትራንስፖርት ዘርፍ ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው ስራ አለመሆኑን በመግለፅ፤ ቅንጅታዊ አሰራን በማጠናክር በክፍለ ከተማው የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ በአፅንኦት ገልፀዋል።
የታክሲ ተራ ማስከበር ማህበራትም በአንዳንድ አባላት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዳሉ ገልፀው፤ በቀጣይ ከአባላቱ ጋር በመመካከርና ችግሮቹን በማረም የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን የተሻለ ለማድረግ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።
በውይይቱም የቦሌ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት፣ የክፍለ ከተማው ሰላምና ፀጥታ ቢሮ፣ ስራ እድል ፈጠራ፣ የትራፊክ ፖሊስ መምሪያ፣ የታክሲ ተራ አስከባሪ ማህበራት ተሳታፊ ሆነዋል።