አዲስ አበባ፤ ህዳር 24፤ 2015 ዓ.ም፤ የትራንስፖርት ሠራተኞችን እና የባላድርሻ አካላትን የመፈፀም አቅም ለማሳደግ በትራንስፖርት ህግ ማስከበር እና ተያያዥ የአሰራር መመሪያዎች ዙሪያ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ የቦሌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ምስራቅ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ስልጠናውን አዘጋጅተዋል፡፡
በአቅም ማጎልበቻውም የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ሚና የጎላ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የቦሌ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ አበባው ታከለ ስልጠናው ባለድርሻ አካላት ተናበውና ተቀናጅተው እንዲሰሩ የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለውና ተገልጋዩን ህብረተሰብ በቅንነት ለማገልገል ውጤት የሚመጣበትን አሰራር በመፍጠር መልካም ሥነ-ምግባር ያላቸው ሠራተኞችን እና ባለድርሻ አካላትን ለማበራከት ይረዳል ብለዋል፡፡
የስልጠናውን ግምገማዊ ሰነድ ያቀረቡት የቦሌ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የትራንስፖርት ሰምሪትና ድልድል ዳይሬክተር አቶ ወርቁ ተሾመ በበኩላቸው የትራንስፖርት ሠራተኞችን እና የባለድርሻ አካላት ሚና ለማሳደግ ስልጠናው እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡
በመጨረሻም የመረጃ ተደራሽነትን ከማሳደግ አኳያ፣ የቁጥጥር ስራዎችን ለማጠናከር የማዘመን ስራዎች፣ የህግ አስፈፃሚ አካላትን በተለይ የቁጥጥር ሠራተኞችን በተከታታይነት አቅም ከማሳደግ አንፃር በትኩረት መሰራት እንዳለበት የስልጠናው ተሳታፊዎች ገልፀዋል፡፡
በስልጠናውም የቦሌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ትራንስፖርት ሠራተኞች፣ የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የምሰራቅ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት፣ ከቦሌ ፖሊስ መምሪያ፣ ከተራ ማስከበር ማህበራት፣ ከታክሲ ባለንብረቶች ማህበራት፣ ከደንብ ማስከበር፣ ከንግድ ጽ/ቤት፣ ከስራ እድል ፈጠራ እና ከመሳሰሉት ባለድርሻ ተቋማት የመጡ አመራርና ሠራተኞች ተሳትፈውበታል፡፡