መጋቢት 08/2015ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ የባለሶስት እና አራት እግር (ባጃጅ) ተሽከርካዎች የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ባወጣው መመሪያ ብቻ ከነገ መጋቢት 09/2015ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ቢሮው ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አሳውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የከተማዋ የትራንስፖርት ፖሊሲና ስትራቴጂ የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎትን እንደማያበረታታ በመግለፅ፤ ሆኖም በከተማዋ እየሰጡ ያሉትን አገልግሎት ከግምት ውስጥ በማስገባት ቢሮው የአገልግሎት አሰጣጥ፣ አደረጃጀትና የአሰራር መመሪያ ማዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡
በመግለጫውም ቢሮ ከዚህ ቀደም አገልግሎቱን እየሰጡ ባሉ ስምንት ክፍለከተሞች በ123 ማህበራት 9,550 የባጃጅ ተሽከርካሪዎች መደራጀታቸውን ገልጾ፤ አገልግሎት የሚሰጡበት የስምሪት መስመሮችም በከተማዋ ዳርቻዎችና አዋሳኝ አካባቢዎች፣ በሰፋፊ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሳይቶች እና በተለዩ አንዳንድ የከተማው የውስጥ ለውስጥ አጫጭር መንገዶች ላይ የተወሰነ ሲሆን፤ በዚህ ስምሪት ስርዓት ውስጥ መሳተፍ የሚችሉት ኮድ 1 ሰሌዳ ያላቸው ባለሦስት እና ባለአራት እግር በተለምዶ ባጃጅ ተብለው የሚጠሩ ተሸከርካሪዎች ብቻ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የቢሮ ኃላፊው አክለውም አገልግሎቱን መስጠት የሚችሉት ከጠዋቱ 12፡00 እስከ ምሽት 3፡00 ቢሮው ባስቀመጠው ህጋዊ የታሪፍ መጠን ከ0.9 እስከ 2.5 ኪሎ ሜትር በሁሉም ቦታዎች ተመሳሳይ በሆነ አምስት ብር የታሪፍ ተመን ( 5 ብር ) ሲሆን የመጫን አቅማቸው ሹፌሩን ጨምሮ 4 ሰው ብቻ ነው ብለዋል፡፡
አገልግሎት ሰጪ አሽከርካሪዎችም ቢሮው በሚያወጣው የአሰራር መመሪያ በሙያዊ ስነምግባር ህጋዊ ሆነው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልፀው ይህንን ተላልፈው በሚገኙ አገልግሎት ሰጪዎች ላይ አምስት የጥፋት እርከኖች የተቀመጡ ሲሆን ደረጃ አንድ 200 ብር፣ ደረጃ ሁለት 500ብር፣ ደረጃ ሶስት 1000 ብር፣ ደረጃ አራት ብር 2000 እንዲሁም ደረጃ አምስት ፍቃድን ማሰረዝ መሆኑ በጋዜጣዊ መግለጫው ተገልጿል፡፡