የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ከብሉምበርግ ኢንሸቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ ጋር በመተባበር በሀገርና በከተማ ደረጃ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በዘርፉ ከሚሰሩ ባለድርሻ አከላት ጋር በመንገድ ደህንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች ተደራሽ የሚያደርጉባቸው የሚዲያ ስነ-ተግባቦት አማራጮች እና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ዛሬ በጋራ መከረ፡፡
በውይይቱም በመንገድ ደህንነት ዙሪያ ለህብረተሰቡ በምን አይነትና በየትኛው የስነ-ተግባቦት (ኮሙኒኬሽን) አማራጮች፣ እንዴት ግንዛቤን ተደራሽ ማድረግ እና ንቅናቄን በመፍጠር በሰው ህይወት ላይ የሚደርሰው የትራፊክ አደጋ መቀነስ እንደሚገባ በአፍሪካ የትራንስፖርት ወሳኝ እስትራቴጅዎች እና ግምገማ ኤጀንሲ ቴክኒካል አማካሪ ወ/ሮ አስምረት ንጉሴ
ተገልፆል።
በተጨማሪም የብሉምበርግ ኢንሸቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ የዳታና ሰርቪላንስ አስተባባሪ ወ/ሮ ሜሮን ጌታቸው የ2014 ዓ/ም ዓመታዊ የመንገድ ደህንነት ሪፖርት በዝርዝር አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች አቶ አማረ ታረቀኝ እና ኢንጅነር ኤልያስ ዘርጋ የመንገድ ደህነትን ለማረጋገጥ የስነተግባቦት ስራዎችን በስፋት ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድርግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባና ውጤት ያለውስራ ለመስራት የሁሉም ባለድርሻ አከላት ሚናና ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ መሆኑን በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡
በመጨርሻም የውይይቱ ተሳታፊዎች የመንገድ ደህንነትን ለማስጠበቅ የአደጋ ምንጮችን መለየት፣ የአደጋ መንስኤዎችን ለመቅረፍ የሚሰሩ ስራዎች፣ የመንገድ ደህንነቱ የሚሰጥበትን ቦታዎች፣ የስነተግባቦት የሚዲያ አማራጮች፣ የበጀት አቅርቦት እና የሚዲያ ዘመቻዎች ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ የጋራ ግንዛቤ ወስደዋል።
በውይይቱም የትራንስፖርት ቢሮ፣ ብሉምበርግ ኢንሸቲፍ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ፣ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ፣ ቫይታል እስትራቴጂ፣ የመንገድ ደህንነት መድን ፈንድ አገልግሎት እና በዘርፍ የሚሰሩ ሌሎች ባለድርሻ አካላቶች ተሳታፊ ሆነዋል።