አዲስ አበባ፤ መጋቢት 15፤ 2015 ዓ.ም፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ በከተማዋ በሚስተዋሉ ወቅታዊ በባጃጅና የትራንስፖርት ችግሮች እንዲሁም አሁናዊ ሁናቴና መፍትሔዎች ዙሪያ ዘርፉ ከሚመለከታቸው ሴክተር ተቋማት፤ ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ውይይት አካሂዷል፡፡
በውይይቱም በትራንስፖርት ዙሪያ ከሚስተዋሉ ችግሮች ውስጥ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፣ የትራፊክ ፍሰት መስተጓጎል /የትራፊክ ጃም/ መኖር፣ ህገ-ወጥ የህዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች መበራከት፣ አሽከርካሪና ተሽከርካሪ ላይ ከፍተኛ የሆነ የቅጣት ሰሌዳና መንጃ ፈቃድ ክምችት መኖር፣ በሁሉም አካባቢ መመሪያውን እኩል ተግባራዊ አለማድረግ እና ሌሎች በዘርፉ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች ተነስተዋል::
እነዚህን ችግሮችን ሁሉም የሚመለከታቸው የተቋም አመራርና ባለድርሻ አካላት በተለይ ደግሞ የዘርፉ ባለሙያዎች ትልቅ ሃላፊነት በመውሰድ በጋራና በህብረት ቅንጅታዊ አሰራርን በማጎልበት ከመቼውም በላይ በትኩረት መሠራት እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም በሰሞኑን እንደ ችግር እየተነሳ ያለው የባጃጅ ጉዳይ መመሪያውንና ህግን መሠረት በማድረግ ትራንስፖርት ቢሮው በሰጠው አቅጣጫ መሠረት በተሰጣቸው የስምሪት መስመርና ታሪፍ ሊሰሩ እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡
ይህንን በማይተገብሩ የባጃጅ አሽከርካሪዎች ላይ ቢሮውና የሚመለከተው አካል ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድም የትራንስፖርት ቢሮ ኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሃላፊ ኢንጂነር ዳዊት ዘለቀ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡
ኢንጂነር ዳዊት አያይዘውም ማንኛውም ህጋዊ ባጃጅ ከ2.5 ኪሎ ሜትር በላይ መንቀሳቀስ፣ አደባባይ ማቋረጥ፣ ከ5 ብር በላይ ታሪፍ ማስከፈል እንደሌለባቸው አውቀው በተቀመጠው ርቀት ውስጥ ብቻ መስራት እንዳለባቸው በአንክሮ ገልፀዋል፡፡
በቢሮው ህጋዊ እውቅና ሳይኖራቸው የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጡ የተገኙ የባጃጅ አሽከርካሪዎች ላይ ቢሮው ከፍተኛውን ቅጣት እንደሚወስድ አውቀው ከዚህ ህገ-ወጥ ድርጊታቸው እንዲቆጡም አሳስበዋል፡፡
ምክትል ቢሮ ኃላፊው አክለውም በተመሳሳይ የዳማስ አሽከርካሪዎችም በዚሁ ህግ እንደሚዳኙ አውቀው ህጋዊ እስካልሆኑ ድረስ ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው አሳውቀዋል፡፡
በውይይቱም የ11ዱም ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጆች፣ የከተማዋ የትራፊክ ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች፣ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ፣ የአዲስ አበባ አሽከርካሪና ተሸከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አመራሮች ተሳታፈ ሆነዋል፡፡
ዘገባው፡-በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነው፡፡
ለበለጠ መረጃ፡- 011-666-3374 ወይም ነፃ የስልክ መስመር 9417 ይጠቀሙ!